የመጀመርያው የሴት አሰልጣኞች ስልጠና እየተካሄደ ይገኛል

በኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና በካፍ አማካኝነት የተዘጋጀው በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በኢትዮዽያ የመጀመርያው ለሴቶች የሚሰጥ C ላይሰንስ ስልጠና በአምቦ ጎል ፕሮጀክት መሰጠት ተጀመረ፡፡

ከትላንት በስቲያ በአምቦ ከተማ ጎል ፕሮጀክት አካዳሚ አዳራሽ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደት አቶ ጁነይዲ ባሻ ፣ የስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ እንዲሁም ሌሎች እንግዶች በተገኙበት በይፋ የጀመረው ስልጠና ለ15 ቀናት የሚቆይ ሲሆን ስልጠናው በምስራቅ አፍሪካ እንዲሁም በኢትዮዽያ ታሪክ ለሴቶች የተዘጋጀ የመጀርያው የ C ላይሰንስ ስልጠና ነው፡፡ ስልጠናውን የሚሰጡት አሰልጣኞች ኢትዮዽያውያን ሲሆኑ  ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ፣ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ፣ ኢንስትራክተር መሰረት ማኒ ፣ ኢንስትራክተር መስከረም ታደሰ እና ኢንስትራክተር ሰላም ዘራይ ናቸው። ስልጠናውን የሚካፈሉትም ቁጥራቸው 36 የሚሆኑ የቀድሞ ሴት ተጨዋቾች ፣ አሁን በመጫወት ላይ የሚገኙ እና ቀድመው በማሰልጠን ላይ የሚገኙ ሰልጣኞች ይሆናሉ።

በስልጠናው በባለሙያዎች የተደራጀ መሰረታዊ የአሰለጣጠን ስልጠና እና ትምህርት የሚሰጣቸው ሲሆን ለስልጠናው አሰፈላጊ የሆኑ ነገሮችን በሙሉ በመሸፈን የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ድጋፍ ያደረገ መሆኑን ለማወቅ ችለናል ።

በስልጠናው ላይ በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝንደት አቶ ጁነይዲ ባሻ በምስራቅ አፍሪካ የመጀመርያው ስልጠና እንደሆነና ለሴቶች ከዚህ በተሻለ ድጋፎችን እንደሚያደርጉ ፤ ፌዴሬሽኑም በሁሉም ነገር  ከጎናቸው እንደሚቆም ገልፀው መልካም የስልጠና ጊዜ እንዲሆን በመመኘት ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

በስልጠናው አጠቃላይ ጠቀሜታ ዙርያ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረገችው ስልጠናውን በመስጠት ላይ ከሚገኙት ኢንስትራክተር አንዱ የሆነችው ኢንስትራክተር መሰረት ማኒ ” እንደሚታወቀው በኢትዮዽያ እግር ኳስ የሴቶች አሰልጣኞች ቁጥር አነስተኛ ነው። ይህ ስልጠና የሴቶች አሰልጣኞች ቁጥር ለመጨመር እና የሴቶች እግር ኳስ እየተስፋፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በፕሪምየር ሊጉ ብቻ 20 ቡድኖች አሉ ወደፊትም ከዚህ በላይ ቁጥራቸው ይጨምራል፡፡ ስለዚህ ሴቶች እህቶቻችን ኳስን ለመጫወት ብቻ ሳይሆን በማሰልጠኑም ቢሆን  ጥሩ አቅም ያላቸው አሰልጣኞችን ለክለቦችም ለሀገሪቱም የሚጠቅሙ ብቁ አሰልጣኞች የሚወጡበት በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡” በማለት ተነግራለች ።

የመጀመርያው የ C ላይሰንስ ለአስራ አምስት ቀን ከተሰጠ በኋላ ለሁለተኛው የ B ላይሰንስ ከሁለት አመት በኋላ የሚሰጥ መሆኑን ለማወቅ ችለናል ።

1 Comment

Leave a Reply