ጥሎ ማለፍ | ጅማ አባቡና እና ወላይታ ድቻ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል

ትላናት በአዲስ አበባ ስታድየም መደረግ የነበረባቸው ሁለት የጥሎ ማለፍ ሩብ ፍጻሜ ጨዋታዎች የአአ ስታድየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ለሚያደርገው የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ ምቹ ለማድረግ በሚል ወደ ዛሬ በመሸጋገር ሰበታ ላይ ተካሂደው ጅማ አባ ቡና እና ወላይታ ድቻ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅለዋል፡፡

04:00 በተደረገው የዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ ጅማ አባቡና ከ አአ ከተማ ተጫውተው በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 0-0 በማጠናቀቃቸው አሸናፊውን ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምት ጅማ አባቡና 5-4 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜው መግባቱን አረጋግጧል ።

ብዙም ማራኪ ያልነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኳስን በሁሉም የሜዳ ክፍል ተቆጣጥሮ ለመጫወት ከተደረገ ጥረት ውጭ በዘጠና ደቂቃ የጨዋታ እንቅስቃሴ ውስጥ ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ጠንካራ የጎል ሙከራ መመልከት አልቻልንም። በጨዋታው ወደ ፍፁም ቅጣት ምት ሊያመራ እንደሚችል የተረዱት የጅማ አባቡና አሰልጣኝ ገብረ መድህን ሀይሌ ለፍፁም ቅጣት ምቱ ይረዳቸው ዘንድ የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ ጀማል ጣሰውን አስወጥተው ሲሳይ ባንጫን ቀይረው  ማስገባታቸው ውጤታማ አድርጓቸው ቀይረው ያስገቡት ሲሳይ ባንጫ ፍፁም ቅጣት ምት የማዳን ብቃቱን ተጠቅሞ ጅማ አባቡና በመለያ ምት በማሸነፍ ግማሽ ፍፃሜውን መቀላቀል ችሏል።

ዛሬ የጅማ አባቡናው አሰልጣኝ ገብረመድን ያደረጉት ጀማል ጣሰውን በሲሳይ ባንጫ ቀይሮ በፍፁም ቅጣት ምት ማሸነፋቸው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ለቻን ውድድር ለማለፍ ሩዋንዳን ሲያሸንፍ በተመሳሳይ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ጀማል ጣሰውን በሲሳይ ባንጫ ቀይረው በማስገባታቸው መሆኑ የሚታወስ ነው ።

06:00 በቀጠለው ሁለተኛው የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ኢትዮ ኤሌትሪክን ከ ወላይታ ድቻ ሲያገናኝ ጨዋታው ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት በሁለቱም በኩል ግልፅ የጎል እድል የተፈጠረበት ወላይታ ከኤሌትሪክ በተሻለ ጫና ፈጥሮ የተጫወተበት ማራኪ ጨዋታ ቢታይበትም እንደመጀመርያው ሁሉ ያለ ግብ መደበኛው ክፍለጊዜ ተጠናቋል፡፡

ጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ግብ ጠባቂውን ወንደሰን አሸናፊን በወንደሰን ገረመው በመቀየር ያደረጉት ለውጥ ተሳክቶላቸው በመለያ ምቶቹ የወንደሰን ገረመው ልዩ ብቃት ታክሎበት ወላይታ ድቻ 4-3 አሸንፎ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅሏል፡፡

የግማሽ ፍፃሜው ውድድር ሰኞ ሲደረግ ወልድያ ከ መከላከያ ፤ ወላይታ ድቻ ከ ጅማ አባቡና የሚጫወቱ ይሆናል፡፡

Leave a Reply