“የማሸነፍ ጫናው ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ነው” የማሜሎዲ ሰንዳውንስ አሰልጣኝ ፒትሶ ሞሲማኔ

በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ አምስተኛ ጨዋታዎች ከአርብ ጀምሮ መደረግ ሲጀምሩ በምድብ ሶስት የሚገኘው የኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ የወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒዮኑን ማሜሎዲ ሰንዳውንስ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ቅዳሜ 10 ላይ ያስተናግዳል፡፡ ጨዋታው በሱፐርስፖርት 4 እና ቤን ስፖርትስ 5 የቀጥታ የስርጭት ሽፋን የሚያገኝ ሲሆን ሁለቱም ክለቦች በእኩል ነጥብ ላይ ተገኝተው ተፋጠዋል፡፡

የ2016 የካፍ ግሎ ሽልማት የአፍሪካ የአመቱ ምርጥ አሰልጣኝ ዘርፍ ያሸነፉት ፒትሶ ሞሲማኔ ስለጨዋታው፣ ስለዝግጅት፣ ጉዳት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለጋዜጠኞች ዛሬ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ሰጥተዋል፡፡

ስለዝናባማው የአየር ሁኔታ እና የመጫወቻ ሜዳ

“ዝናቡን እንደምክንያት ማቅረብ አልፈልግም፡፡ ዝናቡ የሚዘንበው ለእኛም ለቅዱስ ጊዮርጊስም ነው፡፡ በዚህ ላይ ሰበብ መደርደር አይገባም፡፡ ሐሙስ በትምህርት ቤት ሜዳ (የአሜሪካን ትምህርት ቤት ሜዳ) ነበር ልምምዳችንን የሰራነው፡፡ የእግርኳስ ተጫዋቾች በየትኛውም የአየር ሁኔታ መጫወት መቻል አለበት፡፡ ዝናቡ ለሁለቱም ክለቦች ነው የሚዘንበው ስለዚህም የመጫወቻ ሜዳውም እንደዛው፡፡ ከዚህ በላይ መሻሻል ይችላል ግን እኛ ምንም ማድረግ አንችልም፡፡”

በካፍ ማስጠንቀቂያ ስለተሰጠው የአዲስ አበባ ስታዲየም መጫወቻ ሜዳ

“ካፍ ሜዳው ጥሩ አይደለም ካለ እኛን እዚ ለምን ያመጣናል ወይም እኛን ወደ ሌላ የመጫወቻ ሜዳ  መውሰድ ነበረባቸው፡፡ ስለሜዳው ማውራት አንፈልግም ስለጨዋታው ነው ማውራት የምንፈልገው፡፡”

ስለጉዳት እና ከቡድኑ ጋር ስለተለያየው ፈጣሪ አማካዩ ቴኮ ሞዲሴ

“ሁለት ወይም ሶስት የሚሆኑ ተጫዋቾች አብረውን አይደሉም (ካማ ቢሊያት እና ሪካርዶ ናሲሜንቶን ጨምሮ)፡፡ ነገር ግን 11 ጤነኛ ቋሚ ተሰላፊዎች አሉን፡፡ ካማ ቢሊያትም በጉዳት አብሮን እዚህ አይገኝም፡፡ እግርኳስ ስፖርት ነው ተጫዋቾች ይጎዳሉ፡፡ ቡድኑ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል፡፡ ተፅዕኖው ምን ያህል ነው የሚለውን ላናውቅ እንችላለን፡፡ ቱኒዝ ላይ ከኤስፔራንስ ጋር ስንጫወት የተጎዱት ተጫዋቾች አልነበሩም፡፡ ይህ ሰበብ አይሆንም፡፡”

“የቴኮ ሞዲሴን ጉዳይ ልክ እንደተጎዳ ተጫዋች ነው የማየው፡፡ አንዳንድ ግዜ የሚፈጠሩ ነገሮችን እንደዛ ነው የማያቸው፡፡ ቡድኑ ላይም ምንም ጉዳት አያመጣም፡፡”

ስለጨዋታው

“ወደ ቱኒዝ ተጉዘን ከኤስፔራንስ ላይ ያሳካነው አንድ ነጥብ ለእኛ በጣም ወሳኝ ነበር፡፡ ቱኒዝ ለማሸነፍ ከሚከብዱ ቦታዎች መካከል ነች ጊዮርጊስ ደግሞ የመጨረሻ ጨዋታውን ቱኒዝ ነው የሚያደርገው፡፡ በጣም ከባድ ጨዋታ እንደሚሆን አልጠራጠርም ቢሆንም የማሸነፍ ጫናው ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም በደረጃ ሰንጠረዡ ከእኛ በታች ናቸው፡፡ ስለዚህም ጨዋታው የግድ ማሸነፍ ስላለባቸው ጫናው እነርሱ ላይ ነው፡፡ ምንአልባትም እኛ ላይ ጫናው ቀለለ ነው ምክንያቱም ካላሸነፉን በደረጃ ሰንጠረዡ ላይ ያለንበት ላይ ነው የምንረጋው፡፡”

ስለ ሳላዲን ሰዒድ

“ለቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ነው፡፡ ልምድ ያለው፣ ከሃገሩ ውጪ የተጫወተ እና ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች ነው፡፡ ስለዚህም ሳላዲን እኛ ልንጠንቀቀው ያስፈልጋል፡፡ ሁሌም በጥንቃቄ ልንመለከተው ይገባል፡፡ ሰባት ግቦችን አስቆጥሯል ከሰንዳውንስ እና ከኤስፔራንስ ጋር ግን ግብ አላስቆጠረም ነገርግን ጥሩ ተጫዋች ስለሆነ እናከብረዋለን፡፡”

Leave a Reply