” ከሰንዳውንስ ላይ ሶስት ነጥብ ማሳካት እንችላለን ” ያስር ሙገርዋ

ዩጋንዳዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ አማካይ ያስር ሙገርዋ ክለቡ በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ አምስተኛ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ የወቅቱ አፍሪካ ቻምፒዮኑን ማሜሎዲ ሰንዳውንስን የሚያስተናግድበትን ጨዋታ እንደሚያሸንፍ ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ሌላኛውን የደቡብ አፍሪካ ክለብ ኦርላንዶ ፓይሬትስን ለቆ ፈረሰኞቹን በአመቱ መጀመሪያ የተቀላቀለው ያስር ጨዋታው ለሁለቱም ክለቦች ፈታኝ እንደሚሆን ጠቁሟል፡፡ “ጨዋታው በጣም ከባድ እና ውድድር ያለበት ይሆናል፡፡ ነገር ግን ከሰንዳውንስ ላይ ሶስት ነጥብ ማሳካት እንደምንችል ተስፋ አለኝ ፡፡”

ሁለቱም ክለቦች በምድብ 3 በእኩል አምስት ነጥብ ወደ ሩብ ፍፃሜ የሚያደርጉትን ጉዞ ለማሳመር የተፋጠጡ ሲሆን የቅዱስ ጊዮርጊስን የግብ ክልል ከ11 ዓመት በፊት የጠበቀው የዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ዴኒስ ኦኒያንጎ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ የቀድሞ ክለቡን ይገጥማል፡፡ ፕሪቶሪያ ላይ በነበረው ጨዋታ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ የነበረው ኦኒያንጎ ከሃገሩ ልጅ ያስር ሙገሳን ቢያገኝም በጨዋታው የፈረሰኞቹ ተጫዋቾች ኦኒያንጎን መፈተን እንደሚችሉ ያምናል፡፡ “እሱን (ኦኒያንጎ) የመሰለ ግብ ጠባቂን ተቃራኒ ሆኜ መግጠሜ ደስታን ይፈጥርልኛል፡፡ ቢሆንም የዴኒስን ደካማ ጎኖች እና እሱን እንዴት ማሸነፍ እንደሚቻል ቀላል ባይሆንም አውቃለው ምክንያቱም አብረን በብሄራዊ ቡድን መጫወት መቻላችን፡፡”

የቀድሞ የዩጋንዳ ረቨንዩ ኦቶሪቲ ተጫዋች በቅዱስ ጊዮርጊስ እንደተጠበቀው ባይንቀሳቀስም ከክለቡ ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ማሸነፍ ችሏል፡፡ “አሰልጣኞቼ እንዴት እየተጫወትኩ እንደነበር አይተዋል፡፡ ተስፋ አለኝ ጨዋታውን መጀመር ከቻልኩ የቻልኩትን እንደማደርግ፡፡ በሚገባ ስለተዘጋጀው በጨዋታው ጥሩ እንደምንቀሳቀስ እምነት አለኝ፡፡”

Leave a Reply