የቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የምድብ አምስተኛ ጨዋታዎች አርብ ምሽት በተደረጉ ሁለት ግጥሚያዎች ሲጀመሩ በኦምዱሩማን ደርቢ የከተማ ተቀናቃኙን አል ሂላልን ያስተናገደው ኤል ሜሪክ ሲያሸንፍ ሴፋክስ ላይ አል አሃሊ ትሪፖሊ ከ ዩኤስኤም አልጀር ነጥብ ተጋርተዋል፡፡
የኦምዱሩማን ደርቢ በኤል ሜሪክ 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ፊፋ በምርጫ ተሸንፈው ከስልጣኛቸው የለቀቁትን ሱዳን እግርኳስ ማህበር ወደ ስልጣናቸው እንዲመለሱ ቀን ቀደብ ማስቀመጡ እንዲሁም ይህ ተፈፃሚ ካልሆነ ሱዳን ከማንኛው የእግርኳስ እንቅስቃሴ እንደምትታገድ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ሁለቱ የሱዳን ሃያል ክለቦች በቻምፒየንስ ሊግ ያላቸው ቆይታ አጠራጣሪ ቢያደርገውም ጨዋታው ለመከታተል በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች በሜሪክ ስታዲየም ተገኝተዋል፡፡ በጨዋታው ሁለቱም ክለቦች በርካታ የግብ እድሎችን መፍጠር ችለው የነበረ ሲሆን በ9ኛው ደቂቃ መሃመድ አብደልራህማን ሜሪክን ቀዳሚ ያደረገች ግሩም ግብ ሲያስቆጥር በሁለተኛው አጋማሽ አብደልራህማን የሜሪክን መሪነት ወደ ሁለት አስፍቷል፡፡ ሙሃናድ ሙሳ አል ሂላልን ከመሸነፍ ያላደነች ግብ በ65ኛው ደቂቃ አስገኝቷል፡፡ ድሉን ተከትሎ ሜሪክ ወደ ሩብ ፍፃሜ ለመግባት መንገዱን ሲመቻች ምን ጨዋታ ማሸነፍ ያልቻለው አል ሂላል አጣብቂኝ ወስጥ ገብቷል፡፡ ምድብ 1 አሁንም ኤትዋል ደ ሳህል በ8 ነጥብ ሲመራ ሜሪክ በ7 ይከተላል፡፡
በቱኒዚያዋ ሴፋክስ ከተማ አል አሃሊ ትሪፖሊ ዩኤስኤም አልጀርን አስተናግዶ 1-1 ተለያይቷል፡፡ ጨዋታው ኢትዮጵያዊያኖቹ ዳኞች ባምላክ ተሰማ፣ ተመስገን ሳሙኤል፣ ክንዴ ሙሴ እና በላይ ታደሰ የመሩት ሲሆን ባለሜዳው ክለብ በርካታ ሙከራዎችን እና የፍፁም ቅጣት ምትን አምክነዋል፡፡ የአልጀርሱ ክለብ ግብ ጠባቂ መሃመድ ዘማሙሺ በርካታ እድሎችን በማዳን የጨዋታው ኮከብ ሆኖ አምሽቷል፡፡ ፋሩክ ቻፊ በ16ኛው ደቂቃ የአሃሊ ትሪፖሊ ተከላካዮች በአግባቡ መከላከል የተሳናቸውን የማዕዘን ምት አስቆጥሮ ዩኤስኤምን ቀዳሚ ሲያርግ አኒስ ሳልቶ በ38ኛው ደቂቃ ሁለት ተከላካዮችን አልፎ የሊቢያውን ክለብ አቻ አድርጓል፡፡ ሁለተኛው 45 ከተጀመረ አራት ደቂቃዎች በኃላ ኢትዮጵያዊው አርቢትር ባምላክ የዩኤስኤም ተከላካይ በፍፁም ቅጣት ምት ክልሉ ኳስን በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ሳሜ ደርባሊ መቶ ዘማሙሺ አድኖበታል፡፡ በሁለተኛው 45 የአሃሊ ትሪፖሊ ከተጋጣሚው በሙከራ ረገድ ተሸሎ ታይቷል፡፡ ምድብ ሁለትን አሁንም ዩኤስኤም አልጀር እና አል አሃሊ ትሪፖሊ በእኩል በ8 ነጥብ ይመራሉ፡፡ የአምስት ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኑ ዛማሌክ በ5 ነጥብ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
ዛሬ አምስት ጨዋታዎች ቀጥለው ሲደረጉ አዲስ አበባ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ሲያስተናግድ ኪንሻሳ ላይ ኤኤስ ቪታ ክለብ ኤስፔራንስን የሚገጥምበት ጨዋታ ይጠበቃል፡፡ 10፡00 ሰዓት ላይ የሚደረገው የጊዮርጊስ እና ሰንዳውንስ ጨዋታ በኢቢሲ፣ ሱፐርስፖርት 4 እና ቤን ስፖርትስ 5 የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ያገኛል፡፡
የአርብ ውጤት
ኤል ሜሪክ 2-1 አል ሂላል
አል አሃሊ ትሪፖሊ 1-1 ዩኤስኤም አልጀር
የቅዳሜ ጨዋታ
15፡00 – ክለብ ፌሬቫያሪዮ ደ ቤይራ ከ ኤትዋል ስፖርቲቭ ደ ሳህል
15፡00 – ዛናኮ ከ አል አሃሊ
16፡00 – ኮተን ስፖርት ከ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ
16፡00 – ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (10፡00 ሰዓት በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር)
16፡00 – ኤኤስ ቪታ ክለብ ከ ኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝ
የእሁድ ጨዋታ
15፡00 – ካፕስ ዩናይትድ ከ ዛማሌክ