ዋልያዎቹ በድንቅ እንቅስቃሴ ኬንያን አሸነፉ (የጨዋታ ሪፖርት)

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ2016 በሩዋንዳ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የቻን ውድድር ለማለፍ የሚያደርገውን የቅድመ ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታ በአሸናፊነት ተወጥቷል፡፡

እንደባለፈው ሳምንት ሁሉ ቁጥሩ 100ሺህ የሚጠጋ ደጋፊ በስታድየም ተገኝቶ በተከታተለው ጨዋታ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ በሌሶቶው ጨዋታ የተወሰኑ የተጫዋች ለውጦችን አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡

 

የብሄራዊ ቡድናችን ቋሚ አሰላለፍ ይህንን ይመስል ነበር፡-

ግብ ጠባቂ – ታሪክ ጌትነት

ተከላካዮች – ስዩም ተስፋዬ – አስቻለው ታመነ – ሳላዲን በርጊቾ – ተካልኝ ደጀኔ

አማካዮች – አስቻለው ግርማ – ምንተስኖት አዳነ – ጋቶች ፓኖም – በኃይሉ አሰፋ (አ)

አጥቂዎች – ራምኬ ሎክ – ቢንያም አሰፋ

ጨዋታው ቀዝቀዝ ብሎ የተጀመረ ሲሆን የመጀመርያዎቹን 20 ደቂቃዎች ኢትዮጵያዎች በኳስ ቁጥጥር ኬንያዎች ደግሞ የግብ እድሎችን በመፍጠሩ በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ አሳይተዋል፡፡

በ7ኛው ደቂቃ አጥቂው ኖህ ዋፉላ የመታት ኳስ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡

በ14ኛው ደቂቃ ላይ የግራ መስመር ተከላካዩ አቡድ ኦማር በኃይሉ አሰፋ ላይ በሰራው ጥፋት የመጀመርያውን ቢጫ ካርድ አግኝቷል፡፡

በ20ኛው ደቂቃ ሚካኤል ኦሉንጋ ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነትን አልፎ ወደ ግብ የሞከራትን ኳስ አስቻለው ታመነ ተንሸራቶ ከግብ መስመሩ በግሩም ሁኔታ አውጥቶታል፡፡

በ23ኛው ደቂቃ ቢንያም አሰፋ ከቀኝ መስመር የተሸገረለትን ጥሩ የግብ አጋጣሚ ቢያበላሽም ከግቡ በቅርብ ርቀት የነበረው አስቻለው ግርማ ወደ ግብነት ቀይሯት ኢትዮጵያን መሪ አድርጓል፡፡

በ34ኛው ዲደቂቃ ላይ አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ የመጀመርያ የተጫዋች ቅያሪ ሲያደርጉ አማካዩ ምንተስኖት አዳነን አስወጥተው ፍሬው ሰለሞንን ተክተዋል፡፡

የመጀመርያው አጋማሽ ቀሪ 10 ደቂቃዎች በግብ ሙከራዎች ካለመታጀቡ ውጪ በኢትዮጵያ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቀጥሏል፡፡ የመጀመርያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም በኢትዮጵያ 1-0 መሪነት ተጠናቋል፡፡

በ2ኛው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃ ራምኬ ሎክ ከቀኝ መስመር የፍፁም ቅጣት ምት ጠርዝ ላይ አክርሮ የመታት ኳስ በግቡ አናት ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡

በ47ኛው ደቂቃ ኬንያዎች ከማእዘን ምት በተሸገረ ኳስ አደገኛ የግብ እድል ቢፈጥሩም የግቡ አግዳሚን ታኮ ወጥቷል፡፡

በ55ኛው ደቂቃ ኖህ ዋፉላ የማስጠንቀቅያ ካርድ ሲመዘዝበት በ57ኛው ደቂቃ በኋላ ደግሞ በአሊ አቦንዶ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡ ተቀይሮ የገባው አሊም በአንድ ደቂቃ ልዩነት ከቀን መስመር ወደ ግብ የሞከራት ኳስ ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡

በ65ኛው ደቂቃ ጋቶች ፓኖም ከፍፁም ቅታት ምት ክልል ውጪ ወደ ግብ አክርሮ የመነታው ኳስ በግቡ አናት ወደ ውጪ ወጥታለች፡፡

በ67ኛው ደቂቃ ሃምፍሬይ ኦቺንግ በበጃኮብ ኬሊ ተቀይሮ ወጥቷል፡፡

በ71ኛው ደቂቃ ራምኬ ሎክ በግምት ከ25 ሜትር ወደ ግብ የመታውን ግሩም ኳስ ግብ ጠባቂው ቦንፍሬይ ኦሊች በአስደናቂ ሁኔታ ወደ ውጪ አውጥቷታል፡፡

በ77ኛው ደቂቃ በቢንያም አሰፋ ላይ በተሰራው ጥፋት የተገኘውን የፍፁም ቅታት ምት ጋቶች ፓኖም ወደ ግብነት ለውጧት ኢትዮጵያ 2-0 እንድትመራ አስችሏታል፡፡

የእለቱ አርቢቴር ለኬንያ የፍፁም ቅጣት ምት ሲሰጡ ኢትዮጵያ ግብ ካስቆጠረች ሁለት ደቂ እንኳን አልሞላትም ነበር፡፡ ኬልቪን ኪማኒ የመታውን ፍፁም ቅጣት ምት ግብ ጠባቂው ታሪክ ጌትነት በግሩም ሁኔታ መልሶታል፡፡

በ81ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ ቢንያም አሰፋን ተክቶ ወደ ሜዳ ሲገባ በኃይሉ አሰፋ የማስጠንቀቂያ ካርድ አይቷል፡፡

በ83ኛው ደቂቃ ባዬ ገዛኸኝ ከቀን መስመር መሬት ለመሬት የመታው ኳስ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡

በ84ኛው ደቂቃ ቻርልስ ኦዴቴ ጄስ ዌርን ተክቶ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡

በ85ኛው ደቂቃ ታሪክ ጌትነት በጭንቅላት የተገጨን አደገኛ ኳስ በአስደናቂ ሁኔታ በማውጣት የዋልያዎቹን መሪነት ማስጠበቅ ችሏል፡፡

በ88ኛው ደቂቃ ላይ ተከላካዩ በረከት ቦጋለ ራምኬ ሎክን ተክቶ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡

ኢትዮጵያ በቡድንም ሆነ በግል ምርጥ እንቅስቃሴ ያሳየችበት ጨዋታ በኢትዮጵያ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ በጨዋታው ላይም ፍፁም ቅጣት ምት ጨምሮ አደገኛ ኳሶችን ያዳነው ታሪክ ጌትነት ፣ የመጀመርያ ኢንተርናሽናል ጨዋታውን ደረገው ተካልኝ ደጀኔ ፣ አስቻለከው ግርማ እና አስቻለው ታመነ እንዲሁም ራምኬ ሎክ ድንቅ እንቅስቃሴ አሳይተዋል፡፡

ብሄራዊ ቡድኑ ከ15 ቀናት በኋላ በኬንያ የመልስ ጨዋታውን አድርጎ ወደ ተከታዩ ዙር የሚያሳልፈውን ውጤት ካስመዘገበ በቀጣይ ማጣርያ የቡርንዲ እና ጅቡቲ አሸናፊን ይገጥማል፡፡

ያጋሩ