በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ከምድብ 3 የቱኒዚያው ኤስፔራንስ እና የደቡብ አፍሪካው ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ወደ ሩብ ፍፃሜ ያለፉበትን ውጤት ሲያስመዘግቡ በምድብ ውድድር ለመጀመሪያ ግዜ የተሳተፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኤኤ ቪታ ክለብ ከምድቡ መሰናበታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሜዳው እና ደጋፊው ፊት በማሜሎዲ ሰንዳውንስ 1-0 ሲሸነፍ ኤስፔራንስ ከኃላ ተነስቶ ከቪታ ክለብ ጋር 2-2 ተለያይቷል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የቅዱስ ጊዮርጊስ ምክትል አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ፣ የማሜሎዲ ሰንዳውንስ አሰልጣኝ ፒትሶ ሞሲማኔ፣ የማሸነፊዋን ግብ ያስቆጠረው አንቶኒ ላፎር እና በጨዋታው የፍፁም ቅጣት ምት ያመከነው ዴኒስ ኦኒያንጎ ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
“ለእኔ ከማንም ሰው የበለጠ የዛሬው ሽንፈት ህመም ነው” ፋሲል ተካልኝ
ስለቅያሪዎች
“በሁለተኛው 45 ወደ መጨረሳቹ ደቂቃዎች የበለጠ ማጥቃት ስለፈለግን የአጥቂ ቁጥራችንን ለማብዛት ሞክረናል፡፡ ሰዎች ሁልግዜም ከጨዋታ በኃላ ውጤት ጥሩ ከሆነ ቅያሪው ትክክል ነው ተብሎ የሚታሰበው ውጤት ጥሩ ካልሆነ ደግሞ የአሰልጣኞች ስህተት ተደርጎ ነው ሁልግዜ በእግርኳስ የሚወሰደው፡፡ ለእያንዳንሱ ለቀየርናቸው ተጫዋቾች ሃላፊነቱን እንወስዳለን፡፡ እኛ ካየንበት አንግል ሞክረናል አልተሳካም፡፡”
“የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች ስናስገባ መሃሉ መከፈቱ የታወቀ ነው፡፡ ኒኪማን ወደ ዳር አውጥተናል፡፡ አዳነን አስገብተን ሳላ እንዲደግፍ ለማድረግ ሞክረናል፡፡ በኃላ ደግሞ አዳነን ወደ ግራ አውጥተን ሁለተኛ ሳላዲንን የሚረዳው አጥቂ አስገብተናል፡፡ ይህ ሁሉ የተደረገው ጨዋታውን ለማሸነፍ ነው፡፡ ልምድ ያላቸውን እና በማጥቃቱ ላይ ይረዱናል ያልናቸውን ተጫዋቾች አስገብተናል፡፡ ትክክል ነው ቡድኑ ከእረፍት በኃላ ግብ ስለገባበት አቀያየሩ ስህተት ነው ብሎ ሊያስብ ይችላል፡፡”
እድልን ስለአለመጠቀም
“ለሽንፈቱ ግለሰቦች ላይ ተንተርሼ አስተያየት ባልሰጥ ደስ ይለኛል፡፡ ከሌላው ግዜ በተለየ ዛሬ ጊዮርጊስ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ በአጫጭር ኳስ ለመጫወት ሞክሯል፡፡ እንዳያውም ከሜዳችን ኳስን እየመሰረተ ሲወጣ ነበር፡፡ በመጨረሻው የሜዳ ክልል ላይ ብዙ እድሎች አግኝተናል የፍፁም ቅጣት ምት ሁሉ ስተናል፡፡ ምንአልባት ሽንፈቱን በፍፁም ቅጣት ምት ማያያዝ አልፈልግም ግን ከፍፁም ቅጣት ምቱ በፊት ያገኘናቸው እድሎች ብንጠቀምባቸው ኖሮ ጨዋታውን ማሸነፍ እንችል ነበር፡፡ ሰዓት እያለቀ ሲሄድ የእኛ ተጫዋቾች መጨነቃቸው እነሱ (ሰንዳውንሶች) ደግሞ ከፍ እያሉ መሄዳቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ እነሱ አላማ አርገው የመጡት አንድ ነጥብ ይዞ ለመመለስ ነው፡፡ ወደ መጨረሻ ላይ ግብ ከገባብን በኃላ የተጫዋቾችን መነሳሳት ዝቅ ብሏል፡፡”
የውጤቱ ተፅዕኖ
“እኔ ጊዮርጊስ ተጫውቼ አድጌያለው፡፡ ጊዮርጊስ የቤተሰቤን ያህል ይሰማኛል፡፡ ለእኔ ከማንም ሰው የበለጠ የዛሬው ሽንፈት ህመም ነው፡፡ ያመንበትን አድርገናል፤ ውጤቱ አልተሳካም፡፡ እኛም መውሰድ ያለብንን ሃላፊነት እንወስዳለን፡፡ የእግርኳስ አንዱ ገፅታ ይህ ነው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ለመድረስ ብዙ መልካም ያልሆኑ ግዜያቶች አሳልፈናል፡፡ ይህንን እድልን ስላጣን እውነት ህመም ተሰምቶኛል፡፡”
“እረፍት ላይ ስህተቶቻችንን ለማረም ሞክረናል” ፒትሶ ሞሲማኔ
ስለተሳተው የፍፁም ቅጣት ምት
“እድለኛ ነን ስላመክነው፡፡ እንደምታውቁት ዴኒስ (ኦኒያንጎ) በአፍሪካ የሚጫወት የዓመቱ አፍሪካ ኮከብ ተጫዋች ነው፡፡ ዴኒስ ኳሷ በሄደችበት አቅጣጫ በመውርወሩ አድኖታል፡፡ እግርኳስ እንዲህ ነው አንዳንድ ግዜ ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ትሄዳለህ፡፡ ስለዚህም ወደ ትክክለኛው አቅጣጫ ሆዶ አድኖታል፡፡ ይህ እግርኳስ ነው አንዳንዴ ትንሽ እድል ያስፈልገሃል፡፡ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በእንደዚህ አይነት ግዜያት ቡድናቸውን ማዳን አለባቸው፡፡”
በሁለተኛው አጋማሽ ስለተሻሻለው ቡድናቸው እና ስለሁለተኛው 45
“በመጀመሪያው አጋማሽ እንዲጫወቱ ፈቅደንላቸዋል ማለት አልችልም፡፡ ወደ እኛ የሚመጣውን ሁሉ በአግባቡ መረዳት አለብን፡፡ የሚወጣውን ነገር ካወቅን በኃላ እረፍት ላይ ስህተቶቻችንን ለማረም ሞክረናል፡፡ ለማለፍ የግድ ማሸነፍ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ ስለዚህም ፊት ላይ ሰዎችን ጨምረው ለእኛ ክፍተትን ሰጡን፡፡ ይህ ደግሞ እኛ መሃሉን እንድንቆጣጠር እና ኳስን እንድቀባበል አስቻለን፡፡ ናትናኤል ብቻ ቀርቶ ስለነበር በቀላሉ የመሃልሜዳ ብልጫን ወሰድን፡፡ ልምድም እንዳለን ይታወቃል፡፡ ጨዋታው ከዚህም በላይ ፈጣን መሆን ይችል ነበር ነገርግን ሜዳው ላይ የእኛ ብቻ ሳይሆን የእነሱም ተጫዋቾች እየወደቁ ነበር፡፡ ይህ ጉዳት አለው፡፡ ሜዳው ጥሩ ቢሆን ኖሮ ምንአልባትም ሊያሸንፉ ይችሉ ነበር፡፡ ሜዳው ለሁለታችንም ጥሩ አይደለም፡፡”
ስለቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች
“በሟሟሟቅ ላይ እያለን ያየነው የደጋፊዎች ድባብ ልክ እንደቱሪስት ቆመን ያላቸውን ጥልቅ ስሜት አድንቀናል፡፡ (ፒትሶ በድባቡ ለደጋፊዎቹ ያለቸውን አድናቆት በጭብጨባ ገልፀዋል፡፡) ቆንጆ ነበር፡፡ ይህንን ድባብ ቡድኔ ቢኖረው ኖሮ ቡድኔ ሙሉ ለሙሉ ይለወጥ ነበር፡፡ እውነት ለመናገር በጣም ቆንጆ ነገር ነው የተመለከትነው፡፡”
“ለአሰልጣኞች ቡድን አባላት ነግሪያቸዋለው የዛሬው የደጋፊዎች ድባብ በተጫዋችነቴ በአውሮፓ ያየሁትን ነገር ነው ያስታወሰኝ፡፡ እንደዚህ አይነት ድባብ በቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ዛማሌክን ስንገጥም 70 ሺህ ተመልካቾችን አይተናል፡፡ ይህን ነገር በደቡብ አፍሪካ አንመለከትም፡፡ ተመልሼ መጥቼ የምንጫወትበትን ግዜ እንዲመጣ እመኛለው፡፡”
“ቅዱስ ጊዮርጊስን ብወድም ስራዬን መስራት ነበረብኝ” ዴኒስ ኦኒያንጎ
ስለጨዋታው
“ለእኔ የስራ ጉዳይ ነው፡፡ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ከዚህ በፊት ተጫውቻለው አሁን ደግሞ ተመልሼ ከሰንዳውንስ ጋር መጥቻለው፡፡ ሜዳውን ለመመልከት ስወጣ ደጋፊዎቹ ባደረጉልኝ አቀባበል በጣም አመሰግናለው፡፡ ተመልሼ መምጣቴ ስሜታዊ አርጎኛል፡፡ ግን ስሜቴን ወደ ጎን ትቼ ጨዋታውን መጫወት ነበረብኝ ምከንያቱም ቅዱስ ጊዮርጊስን ብወድም ስራዬን መስራት ነበረብኝ፡፡”
“ሁሌም ድል ማድረግ ጣፋጭ ነው፡፡ እዚ የመጣሁት ለስራ ነው ምክንያቱም ሰንዳውንስ ነው ደሞዝ የሚከፈልኝ፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በጨዋታው ላይ ጥሩ ታግለዋል፡፡ ለማሸነፍም መሞከራቸውን አሳይተዋል፡፡ እኛም ልምዳችን ተጠቅመን ወደ ቀጣዩ ዙር አልፈናል፡፡ ጥሩ ግብ ነው ያስቆጠርነው፡፡ እናውቅ ነበር ክፍተቶች ሲፈጠሩ ግብ አንደምናስቆጥር እናም እድል አግኝተን ተጠቅመንበታል፡፡”
ስለፍፁም ቅጣት ምቱ
“ከልምድ ጋር የሚመጣ ነው፡፡ ከኤስፔራንስ ጋር ላድን አልቻልኩም ነበር፡፡ እኔ እንደማስበው ዛሬ የእኔ ወቅት ነበር፡፡ በእርግጥ እሱ (ሳላዲን) የፍፁም ቅጣት ምት ሲመታ ያየናቸው ምስሎች ብዙ አይደሉም ግን ውሳኔ ወስኟለው፡፡ እኔም ቡድኔን መከላከል ነበረብኝ ይህኔ ገብቶብን ቢሆን ኖሮ ወደ ጨዋታው ለመመስ ይከብደን ነበር፡፡ ይህ በጣም ረድቶናል፡፡”
“ካሸነፍን ወደ ቀጣዩ ዙር እንደምናልፍ እምነት ነበረን” አንቶኒ ላፎር
በቻምፒየንስ ሊግ ሁሉም ጨዋታ ወሳኝ ነው፡፡ ከጨዋታው በፊት አሰልጣኞቻችን ይህ ለመጨረሻ ግዜ የምናገኘው እድል እንደሆነ ነግረውናል፡፡ ካሸነፍን ወደ ቀጣዩ ዙር እንደምናልፍ እምነት ነበረን፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ ጫናው ከፍተኛ ነበር፡፡ እድል አግኝተን ግብ አስቆጥሪያለው፡፡ ይህ ስለእኔ ሳይሆን ስለቡድኑ ነው፡፡ በማሸነፋችን በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ውድድሩ ቀና ብዙ ርቀት ስላለው ጠንክረን መስራት አለብን፡፡ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችን አመሰግናለው ዛሬ እግርኳስን ሲደግፉ ነበር፡፡”