​“ኃላፊነት የሚወስድ አሰልጣኝ ያስፈልገናል ” አቤል ማሞ

ካሜሩኑ በ2019 ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የሚደረገው የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች በሰኔ ወር መጀመሪያ ሲጀመሩ ወደ ኩማሲ አቅንቶ ጋናን የገጠመው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 5-0 በሆነ ሰፊ ውጤት ተሸንፎ የማጣሪያ ጉዞው ጀምሯል፡፡ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ከሽንፈቱ ማግስት ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን በጨዋታው ዙሪያ ሪፖርት ያቀረቡ ሲሆን ለሽንፈቱ ምክንያት ናቸው ያሉትን የጋናዎች በቴክኒክም ሆነ በታክቲክ የነበራቸው ብልጫ እና በጨዋታው የቡድኑ ግብ ጠባቂ አቤል ማሞን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በአፍሪካ ሃገራት ማጣሪያ (ቻን) በአንደኛ ዙር ማጣሪያ ከጅቡቲ ጋር ላለበት ጨዋታ ድሬዳዋ ላይ ዝግጅቱን የጀመረ ሲሆን አቤል ከጋናው ጨዋታ መልስ ከተቀነሱ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ነው፡፡ ሪፖርቱ ብዙዎችን ያነጋገረ ሲሆን ግብ ጠባቂው አቤል በሪፖርቱ ዙሪያ ያለውን ቅሬታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል፡፡



አሰልጣኝ አሸናፊ ከጋናው ሽንፈት መልስ ሪፖርታቸው አቅርበዋል፡፡ በሪፖርቱም ላይ ለሽንፈቱ ምክንያት ካደረጓቸው ጉዳዮች መካከል አንተ አንዱ ነህ፡፡ ይህንን እንዴት ትመለከተዋለህ?

ሪፖርቱ ጨዋታውን በማስከተል የመጣ ነው ፤ ሆኖም ግን ጨዋታው የሚገልፅ አይደለም፡፡ በዚህ ላይ እኔ ራሴ ቅራኔ አለኝ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ሰዓት ራስህን ከሃላፊነት የምታሸሽበት ሳይሆን ከጨዋታ በኃላ ራሳችንን ገምግመን ለቀጣዩ የምናስብበት ነው እንጂ የምንወቃቀስበት መሆን አልነበረበትም፡፡ ሆኖም እሳቸው (አሰልጣኝ አሸናፊ) እራሳቸውን ከሃላፊነት ለመሸሽ ያደረጉት ጥረት ነው፡፡ ጨዋታው ሁሉም ሰው ያየው ነው፤ ይህንን ህዝብ እንዲህ ብለህ ልትሸውደው አትችልም፡፡ ምክንያቱም መዳኘት እና ያየውን መመስከር የሚችል ህዝብ ነው፡፡ ሪፖርቱን ራሱ የተቀበሉት ሰዎች አላውቅም እንዴት እንደተቀበሉት ለእኔ ራሴ ግራ ያጋባኛል፡፡ ሆኖም ግን ትልቅ ባለሙያ ናቸው፤ እንደባለሙያነታቸው ውስጥ ነው እንጂ ቡድንህን የምትሰራው በእንደዚህ ዓይነት ሰዓት ብዙ ቡድኖችም እንዲሁም አሰልጣኞች የሚያደርጉት የተለመደ ነው እኛ ነን ሃላፊነቱን የምንወስደው ነው ሚሉት፡፡ ምክንያቱም ቡድናችን ሙሉ ለሙሉ የተበለጠበት ጨዋታ ነው፡፡ በስህተት እንኳን ግብ ገብቷል የምትልበት ጨዋታ አይደለም፡፡ በጣም የታየ እና ከአቅም በላይ የሆኑ ልንከላከላቸው ያልቻልነው፣ ጨዋታውንም መቀየር ያልቻልነው፣ ትንፋሽ ልንወስድ ያልቻልንበት ጨዋታ ነበር፡፡ ‘እኛ የት አለን?’ ‘ምን ነበር ስንሰራ የነበረው?’ ነው እንጂ የሚባለው አንድ ሰው ላይ ሃላፊነቱን ጭነህ እራስህን ወደ ቀጣይ ስራ ለማዞር ወይም ደግሞ የህዝብን ጫና በመፍራት ብቻ እንደዚህ አይነት ሪፖርቶች መቅረብ የለባቸውም፡፡ ሪፖርቱ ተገቢ አይደለም፡፡ እኔ ተመልሼ ሃገሬን ማገልገል እፈልጋለው፡፡ ይህንን ሪፖርት ስትሰማ  የሚሰማህ ስሜት አለ፡፡ ይህ ስሜት የእኔ ብቻ አይደለም የሚሆነው በዚህ ሰዓት አሁንም በብሄራዊ ቡድኑ ውስጥ በረኞች አሉ፡፡ ነገን ተስፋ አድርገው የሚሰሩ በረኞች አሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ሰበቦች ዛሬ አይደለም ከዚህ በፊትም የነበሩ ናቸው፡፡ ስለዚህ አቅምህን እንዳታወጣ ልትሆን ነው ከእንደዚህ አይነት ቡድኖች ጋር ስትጫወት ምክንያቱም እንደዚህ አይነት ሰበቦች የሚመጡ ከሆነ እንዴት ነው ኳሳችን ሊያድግ የሚችለው፡፡ ሃላፊነት የሚወስድ አሰልጣኝ ነው የሚያስፈልገው በዚህ ሰዓት፡፡ አመቱን ሙሉ ጥሩ ስለተንቀሳቀስኩ ነው የጠራኝ፡፡ ሁላችንም ጥሩ ተንቀሳቅሰን ነው ወደ ብሄራዊ ቡድን የተጠራነው፡፡ የጋናው ጨዋታ ላይ ግን እንደቡድን ጥሩ አልነበርንም፡፡ ነገ አሻሽለን የምንመጣበትን ነው እንጂ መመካከር የነበረብን ሽሽት አያስፈልገውም ነበር፡፡ አሁን በጥሩ ጤና እና ስሜት ላይ ነው የምገኘው ስራዬንም በአግባቡ እየሰራው ነው የምገኘው፡፡


ቡድኑ ጋናን ከመግጠሙ በፊት አዲስ አበባ ላይ ሲዘጋጅ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በጨዋታው ላይ እቅዱ ምን እንደሆነ የማይታወቅ እንዲሁም ዝግጅት እራሱ በቅጡ የሰራ ቡድን አይመስልም፡፡ ቡድኑ በጨዋታው ሙሉ ብልጫ የተወሰደበት መሆኑን እንዲሁም የመካከል አደረጃጀት በጣም የወረደ መሆን በጨዋታው ታይቷል፡፡ ስለቡድኑ የጨዋታ ዝግጁነት፣ በጨዋታው የተጠቀመው አጨዋወት አሁን ከቀረበው ሪፖርት ጋር እንዴት ታነፃፅረዋለህ?

ሶስት ጨዋታ ነው ያደረግነው የወዳጅነት በዛ ላይ ቡድናችን በስነ-ስርዓት አይተነዋል ማለት ይቻላል፡፡ ለሁለት ተከፍለን ነው የወዳጅነት ጨዋታ ስናደርግ የነበረው፡፡ ይህንን ስታይ ለጨዋታው ዝግጁ ሆነናል ብለን ነው የሄድነው፡፡ ሜዳ ውስጥ ከገባን በኃላ የነበረን የአጨዋወት ስርዓት እና የተቃራኒ ቡድን ጥንካሬ ደግሞ እኛ የሰራነው ዝግጅት በቂ እንዳልሆነ ነው ያሳየን፡፡ በተከተልነው የአጨዋወት ዘይቤ አላውቅም ጋናን ልንቋቋመው አልቻልንም፡፡ አሁን ጋና ትልቅ ቡድን ነው አይደለም ከምድብ ለማለፍ ዋንጫ ይበላል ተብሎ የሚጠበቅ ቡድን ነው፡፡ ካለህ ውጪ ሌላ የምታደርገው ዝግጅት የለም፡፡ ያለህ ተጫዋች ላይ ያላቸው ክህሎት ላይ ነው የቡድን አወቃቀር ሊኖርህ የሚገባው እንጂ አምነህ ይህ ስርዓት ውጤታማ ያረገኛል ብለህ የተከተልከው ዘይቤ ተቀይሮ ስታገኘው እኔ አይደለሁም ዓይነት ነገር ማለት ለእኔ ይጋጭብኛል፡፡

ሪፖርቱ ከቀረበ ሁለት ሳምንት አልፎታል፡፡ ለአሰልጣኝ አሸናፊ ቅሬታህን የመግለፅ አጋጣሚ አግኝተሃል?

እሳቸውን ለማግኘት ምንም አላሰብኩም፡፡ ምክንያቱም እርግጠኛ ነኝ ትክክለኛ ሪፖርት አልነበረም፡፡ በተለያዩ ሚዲያዎችም እንዲሁም በህዝቡም በኩል ተገቢ ሪፖርት እንዳልሆነ ሰምቻለው፡፡ እኔ እሳቸውን ማግኘት አይጠበቅብኝም፡፡ ይህ ጥሩ መልስ ነው ለእሳቸው ብዬ አስባለው፡፡ ግን እንደአሰልጣኝ አሁንም ሲቀንሱኝ ምን ዓይነት ጤና ላይ ነህ ምን ላይ ነው ያለኸው አሁንስ ሰላም ነህ ወይም የሚሉትን ነገሮች መጠየቅ አለብን፡፡ እኔ የመጀመሪያ ተሰላፊ በረኛ ነኝ፡፡ በእሳቸው ግዜ ብቻ አይደለም ከእሳቸው በፊትም እኔም በመረጡኝ የመጀመሪያ ተሰላፊ ነበርኩ፡፡ ይህ ስላለ ብቻ ሳይሆን የቡድን ስብስብ ውስጥ እስካለ ድረስ ክብር የሚባለው ነገር መኖር አለበት፡፡ ይህ ተጫዋቾችን ያነሳልም የሚገድልበትም ሁኔታ ሊኖር ይችላል፡፡ እራስህን ብቻ አድምጠህ የምትሄድበት እግርኳስ ሊኖረን አይገባም በእኔ አመለካከት፡፡


በብዛት ለብሄራዊ ቡድን የሚጫወቱ ተጫዋቾች ከአሰልጣኞቻቸው ጋር ቅራኔ ውስጥ ሲገቡ ራሳቸው ከብሄራዊ ቡድን ሲያገሉ ተመልክተናል፡፡ አቤል በቀረበው ሪፖርት ምክንያት ይህንን ያስባል?

እኔ ሙያዬን እወደዋለው ብዙ መስዋትነት የከፈልኩበት ሙያ ነው፡፡ ብዙ ነገሮች ትቼ እዚህ ለመድረስ ረጁም ግዜ አሳልፊያለው፡፡ ከአሰልጣኝ አሸናፊ ጋር በእንደዚህ አይነት ሁኔታ መለያየታችን ትንሽ ያስከፋኛል፡፡ ግን እሳቸው እያሉ ከእሳቸው ጋር አይደለም የእኔ ሙያ፡፡ የእኔ ሙያ ሃገሬን ከማገልገል ጋር ነው፡፡ የእኔ ፍላጎት ብሄራዊ ቡድኔንም ጠቅሜ እራሴም የምጠቀምት ሁኔታ እንዲፈጠር ነው እንጂ በእልህ ምንም አይነት ነገር ውስጥ አልገባም፡፡ እሳቸው የመሰላቸውን አድርገዋል ይህ ደግሞ ተቀባይነት እንዳለው እንደሌለው የታየ ነገር ነው፡፡ እኔ ግን ነገም ዝግጁ ነኝ አይደለም ነገ በአሁኑም ሰዓት ላይ ዝግጁ ነኝ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *