በ23ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ግንቦት 5 ቀን 2009 መቐለ ዩንቨርሲቲ ሜዳ ላይ እየተደረገ በ74ኛው ደቂቃ በደጋፊዎች ረብሻ ምክንያት የተቋረጠው የመቐለ ከተማ እና ባህርዳር ከተማ ቀሪ 16 ደቂቃ ጨዋታ በተለያዩ ምክንያቶች ከ1 ወር በላይ ሳይደረግ ቆይቶ በመጨረሻም በዛሬው እለት 09:00 ላይ በአአ ስታድየም ለደጋፊዎች ዝግ ሆኖ ተካሂዶ ለውጥ ሳይመዘገብበት 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
ግንቦት 5 ላይ በተቋረጠው ጨዋታ ባህርዳር ከተማዎች በቅድሚያ ጎል አስቆጥረው መሪ መሆን ቢችሉም መቐለ ከተማ በፍፁም ቅጣት ምት ጎል አቻ መሆን ችለው ነበር፡፡ ሆኖም ባህርዳሮች ፍጹም ቅጣት ምቱ በተሰጠበት ሒደት ላይ ቅሬታቸውን ሲገልፁ ተከትሎም በስታድየሙ ብጥብጥ በመከሰቱ መቋረጡና ለድርጊቱም ተጠያቂ የተደረጉት ላይ ፌዴሬሽኑ ቅጣት ማስተላለፉ የሚታወስ ነው፡፡
ጨዋታው በዛሬው እለት እንዲደረግ ከሳምንት በፊት የኢትየጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መርሀ ግብር ቢያወጣም እሁድ መቐለ ከ አማራ ውሀ ስራ ያደረገው ጨዋታ በዝናብ ምክንያት ትላንት በማድረጉ በ24 ሰአት ውስጥ ሁለት ጨዋታ ማድረግ የለብንም በማለት በደብዳቤ ጥያቄ ቢያቀርቡም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ትላንት የተካሄደው የሙሉ 90 ደቂቃ ጨዋታ አይደለም በሚል የጨዋታ መርሀ ግብሩ ላይ ለውጥ ሳይደረግበት ዛሬ እንደዲካሄድ ወስኗል፡፡
ዛሬ በጭቃማው አዲስ አበባ ስታድየም በተደረገው የሁለቱ ቡድኖች ቀሪ 16 ደቂቃ ጨዋታ ውዝግቦች የጀመሩት ገና ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ነበር። በባህርዳር ከተማ በኩል ባለ ሜዳው መቐለ ከተማ እንደመሆኑ የመጫወቻ ኳስ አላቀረበም በሚል ጥያቄ ሲያነሱ የመቐለ ከተማ ግብ ጠባቂ ከባህርዳር ከተማ ማልያ ጋር ተመሳሳይ ቀለም በመልበሱ እስኪቀይር ድረስ ጨዋታው ለጥቂት ደቂቃዎች ከሚጀመርበት ሰዓት ተገፍቶ ነበር የጀመረው።
ጨዋታው ከተጀመረ በኃላም የመቐለው ዮሃንስ ፀጋዬ በተቋረጠው ጨዋታ ላይ እንደነበረና መቐለ ከተማ ትላንት ከአማራ ውሀ ስራ ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ በጉዳት በመውጣቱ በተቋረጠው ጨዋታ ላይም መቐለ ከተማዎች የተጨዋች ቅያሬ እንደጨረሱ በመግለፅ ተጫዋቹን ተክቶ የገባው ተጫዋች ተገቢ አይደለም በሚል ባህርዳሮች የክስ ሪዘርቭ አስይዘዋል፡፡
ፌዴራል አርቢትር በፀጋው ሽብሩ በመሩት ጨዋታ ከቀሪው ደቂቃ ማነስ አንፃር በሁለቱም ቡድኖች በኩል የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚዎች አልታዩም። አካላዊ ጉሽሚያዎች በተስተዋለበት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመቐለ ከተማ በኩል ወደ ፕሪምየር ሊጉ አንደኛ ሆኖ ለማለፍ ጨዋታውን ለማሸነፍ ጥልቅ የሜዳ ላይ ፍላጎት ሲያሳዩ ባህርዳር ከተማዎች ደግሞ ቀሪ 16 ደቂቃዋን እና የተጨመረውን 2 ደቂቃ በጥልቀት ሲከላከሉ ተስተውለዋል።
መቐለ ከተማ ከምድቡ መሪ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሰቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት የሚያጠብበትን እና ከመጨረሻው ጨዋታ በፊት በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ የሚያጠብበትን እና በምድቡ አንደኛ ሆኖ የሚያልፍበትን አጋጣሚ ሳይጠቀምበት ቀርቶዋል። በቀጣይ የምድቡ መሪ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሰቲን በሚያስተናግድበት ጨዋታም በቀጥታ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመቀላቀል በ7 የግብ ልዩነት ማሸነፍ ይጠበቅበታል፡፡