የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የዋንጫ እና ወደ ፕሪምየር ሊግ የሚያልፈውን ቡድን የሚለየው ጨዋታ እንዲሁም በአንደኛ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ድሬዳዋ ላይ ከሐምሌ 8 ጀምሮ እንደሚደረጉ ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ 6 ክለቦች ወደ ከፍተኛ ሊጉ መቀላቀላቸውን ያረጋገጡ ሲሆን በስድስቱ ክለቦች መካከል የአንደኛ ሊግ ቻምፒዮን ለመለየት የሚደረገው ውድድር በድሬዳዋ ከተማ ከሐምሌ 8 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 16 ይካሄዳል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ በቀጥታ ለማለፍ የሚደረጉት ወሳኝ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሐምሌ 3 የሚደረጉ ሲሆን አንደኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ክለቦች በቀጥታ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያድጋሉ፡፡ ሁለተኛ ደረጃን ይዘው በማጠናቀቅ 3ኛውን አላፊ ቡድን ለመለየት ወደሚደረገው ጨዋታ የሚያልፉ ቡድኖችም ይለዩበታል፡፡
የአንደኛ ሊጉ በሚካሄድበት ወቅት ሐምሌ 11 ጨዋታ የማይደረግበት ቀን በመሆኑ የከፍተኛ ሊጉ የመጨረሻ ጨዋታዎች በዚህ ቀን የሚደረጉ ይሆናል፡፡ 08:00 ላይ ከየምድባቸው 2ኛ ደረጃ ይዘው የሚያጠናቅቁ ቡድኖች ለደረጃ ሲጫወቱ አሸናፊው ቡድንም 3ኛ ደረጃ ይዞ በማጠናቀቅ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያድጋል፡፡ 10:00 ላይ ደግሞ ምድባቸውን በአንደኝነት የሚያጠናቅቁ ቡድኖች ለከፍተኛ ሊጉ አሸናፊነት ይፋለማሉ፡፡