ኮንፌድሬሽን ዋንጫ፡ ክለብ አፍሪካ እና ፉስ ራባት ሩብ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል

በካፍ ቶታል ኮንፌድሬሽን ዋንጫ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች አርብ ምሽት ሲጀመሩ የቱኒዚያው ክለብ አፍሪካ እና የሞሮኮው ፉስ ራባት ተጋጣሚዎቻቸውን በማሸነፍ ወደ ሩብ ፍፃሜ ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ከምድቡ የማለፍ የተሻለ እድልን ይዞ የተጓዘው የዩጋንዳው ቻምፒዮን ኬሲሲኤ ከሜዳው ውጪ በውድድሩ ያሳየውን ደካማ አቋም በመድገም 4-0 ተሸንፎ ከውድድር ተሰናብቷል፡፡ ፉስ ራበት ሪቨርስ ዩናይትድን 2-1 በመርታት ከምድቡ ያለፈ ሌላኛው ክለብ ሆኗል፡፡

ምድብ አንድ ሁሉም ክለቦች የማለፍ እድል የነበራቸው ሲሆን በተለይ ክለብ አፍሪካ እና ኬሲሲኤ ከቀሪዎቹ ክለቦች በተሻለ የማለፍ እድል ይዘው ወደ ሜዳ ገብተዋል፡፡ ቱኒዝ ላይ በተደረገ ጨዋታ በሁሉም ረገድ የበላይ የነበረው ክለብ አፍሪካ ኬሲሲን 4-0 አሸንፏል፡፡ የሰሜን አፍሪካ በሚታወቁበት የጨዋታ ስልት ተጋጣሚያቸውን ከፍተኛ ጫና ማድረስ የቻሉት ባለሜዳዎቹ በቀድሞ የማርሴ አጥቂ ሳብር ካሊፋ ግብ በ11ኛው ደቂቃ መሪነቱን ጨብጠዋል፡፡ ማኖቢ ሃዳድ ሁለተኛው ግብ በ25ኛው ደቂቃ ከመረብ ሲያዋህድ ለሁለቱም ግቦች መገኘት የቀድሞ የኤስፔራንስ ኮከብ ኦሳማ ዳራጊ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ ዳራጊ ምንም እንኳን በ40ኛው ደቂቃ ተቀይሮ ከሜዳ ቢወጣም ባለሜዳዎቹ የነበራቸውን የመሃል ሜዳ ፍፁማዊ የሆነ ብልጫ ማስቀጠል ችለዋል፡፡ ዳራጊን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሙታዝ ዘምዘሚ በ41ኛው ደቂቃ ልዩነት ወደ 3 ማስፋት የቻለበትን ግብ ከመረብ አዋህዷል፡፡ በፍፁም በጨዋታው ላይ መረጋጋት ያልቻለው የካምፓላው ክለብ አንድ ወርቃማ እድልን በጨዋታው ላይ አግኝቶ የነበረ ቢሆንም ግብ ለማስቆጠር ግን አልታደሉም፡፡

ከኬሲሲኤ ጋር የዩጋንዳ አዛም ፕሪምየር ሊግ እነ የዩጋንዳ ዋንጫን በማሸነፍ የሁለትዮሽ ባለድል የሆኑት አሰልጣኝ ማይክ ሙቲቢ አማካዩን ዴሪክ ኒሲምቢን ወደ ሜዳ ቀይረው ቢያስገቡም ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከብቸው ተስተውሏል፡፡ በሁለተኛው 45 ተጨማሪ የተጫዋቾች ቅያሪን አሰልጣኝ ሙቲቢ ቢያደርጉም ውጤቱን መቀልበስ አልቻሉም፡፡ በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃ ላይ ሳብር ካሊፋ ያሻገረለትን ኳስ ሃዳድ ለራሱ ሁለተኛውን እንዲሁም ለቡድኑ አራተኛው ግብ ግብ ጠባቂውን ቤንጃሚን ኦቻንን ጭምር በማለፍ አስቆጥሯል፡፡ በቱኒዚያ ሊግ 1 የኤስፔራንስ እና ኤትዋል ደ ሳህልን ሃያልነት ሰብሮ መግብት የተሳነው ክለብ አፍሪካ በዘንድሮው የውድድር አመት በሊጉ 3 ደረጃን ይዞ ሲያጠናቅቅ የቱኒዚያ ዋንጫ ባለድል ሆኗል፡፡

በሞሮኮ መዲና ራባት ላይ በተደረገ ጨዋታ ፉስ ራባት ከኃላ በመነሳት የናይጄሪያውን ሪቨርስ ዩናይትድን 2-1 አሸንፏል፡፡ ሁለቱም ክለቦች ማሸነፍ ብቻ ወደ ሩብ ፍፃሜው የሚያበቃቸው በመሆኑ ለመሸናነፍ ከፍተኛ ትግልን አድርገዋል፡፡ በመጀመሪያው 45 በሁለቱም በኩል ጥሩ ጨዋታ የታየ ሲሆን ሳኪን ቦላጂ የፉስ ግብ ጠባቂ የሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ሪቨርስን በ44ኛው ደቂቃ መሪ አድርጓል፡፡ አጣብቂኝ ውስጥ የገቡት ባለሜዳዎቹ ከእረፍት መልስ በተጠናከረ መልኩ የአቻነት ግብ ፍለጋ አጥቅተው መጫወት የቻሉ ሲሆን በ52ኛው ደቂቃ መህዲ ባሲል ከቀኝ መስር ያሻገረውን ኳስ የሱፍ ኤል ጋኑዊ አስቆጥሮ ፉስን አቻ አድርጓል፡፡

ከግቡ መቆጠር በኃላም በተደጋጋሚ የእንግደቹን የተከላካይ መስመር ማስጨነቅ የቻሉት ፉስ ራባቶች የማሸነፊያ ግብ ለማግኘት እስከ88ኛው ደቂቃ መጠበቅ ግድ ብሏቸዋል፡፡ በተለይ ከ80ኛው ደቂቃ በኃላ በሪቨርስ ግብ ጠባቂ እና ተከላካዮች ጥረት ሶስት ያለቀላቸው የግብ እድሎች ግብ ከመሆን ታግደው ነበር፡፡ አካንዴ አቢዮደን ኳስን በፍፁም ቅጣት ምት ክልሉ በእጅ በመንካቱ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት መሃመድ ፋውዚር አስቆጥሮ ፉስን ለወሳኝ ሶስት ነጥብ አብቅቷል፡፡

ምድብ አንድን ክለብ አፍሪካ በ12 ነጥብ በመሪነት ሲያጠናቅቅ ፉስ ራባት በ9 ነጥብ ሁለተኛ ሆኗል፡፡ ኬሲሲኤ 9ኝ ነጥብ ቢኖረውም በግብ ክፍያ እንዲሁም እርስበእርስ ተገናኝተው ለፉስ ራባት የተሻለ ውጤት ስለሌለው ከውድድሩ ተሰናብቷል፡፡ ከናይጄሪያ ፕሪምየር ሊግ ላለመውረድ የሚታገለው ሪቨርስ ዩናይትድ በ6 ነጥብ የምድቡን ግርጌ ይዞ አጠናቋል፡፡

ዛሬ አራት ጨዋታች የሚካሄዱ ሲሆን የምድብ አራት አላፊ ክለቦች የሚታወቁበት ወሳኝ ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ ከምድብ ሁለት አስቀድመው ማለፋቸውን ያረጋገጡት ሴፋክሲየን እና ኤምሲ አልጀር ምድቡን በበላይነት ለማጠናቀቅ የሚያደርጉት ግጥሚያ ይጠበቃል፡፡

የሱዳን እግርኳስ ማህበር በፊፋ በመታገዱ ከምድብ ሶስት ባሳለፍን ሳምንት ወደ ሩብ ፍፃሜ አልፎ የነበረው አል ሂላል ኦባያድ ከምድብ ተሰናብቷል፡፡ ኦባያድ ከዜስኮ ዩናይትድ ጋር ንዶላ ላይ የሚያደርገው ጨዋታም ተሰርዟል፡፡ በፊፋ ቅጣት ምክንያት ሌላኛው የሱዳን ክለብ ኤል ሜሪክ ከምድብ መሰናቱ ይታወሳል፡፡

 

የአርብ ውጤቶች

ክለብ አፍሪካ 4-0 ካምፓላ ሲቲ ካውንስል ኦቶሪቲ

ፋት ዩኒየን ስፖርት 2-1 ሪቨርስ ዩናይትድ

 

የቅዳሜ ጨዋታዎች

14፡30 – ቲፒ ማዜምቤ ከ ሆሮያ አትሌቲክ ክለብ (ስታደ ቲፒ ማዜምቤ)

15፡30 – ሱፐርስፖርት ዩናይትድ ከ ሲኤፍ ሞናና (ሉካስ ማስተርፒስስ ሞርፔ ስታዲየም)

18፡00 – ክለብ ስፖርቲፍ ሴፋክሲየን ከ ሞውሊዲያ ክለብ ደ አልጀር (ስታደ ጣይብ ሚሂሪ)

19፡00 – ፕላቲኒየም ስታርስ ከ ምባባን ስዋሎስ (ሮያል ባፎኬንግ ስታዲየም)

 

የእሁድ ጨዋታ

15፡00- ክለብ ሬክሬቲቮ ዴስፖርቲቮ ዱ ሊቦሎ ከ ስሞሃ (ኢስታዲዮ ደ ካሉሉ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *