“በእግርኳሱ ልንለወጥ የምንችለው ክለቦች ወደራሳችን መመልከት ስንጀምር ነው” – አቶ አሰፋ ሀሊሶ (የወላይታ ድቻ ስራ አስኪያጅ)


ሀሙስ ሰኔ 29 ቀን 2009 በተደረገው የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ ፍፃሜ ወላይታ ድቻ መከላከያን በመለያ ምቶች አሸንፎ የዋንጫ ባለቤት ሆኗል፡፡ በተመሰረተ በ8ኛ አመቱም የመጀመርያውን ትልቅ ዋንጫ ማሳካት እና ለቀጣዩ የውድድር ዘመን የካፍ ኮንፌዴሬሽን ማለፍ ችሏል፡፡ ከድሉ በኋላ የክለቡ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አሰፋ ሀሊሶ ስለ ድሉ ፣ ስለ ወላይታ ድቻ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ወቅታዊ ሁኔታ አስተያየታቸውን ለሶከር ኢትዮጵያ ሰጥተዋል፡፡

ክለቡ በተመሰረተ በ8ኛ አመቱ የመጀመርያውን ዋንጫ አሳክቷል፡፡ ከእድሜው አጭርነት አንፃር ያገኛችሁትን ስኬት እንዴት ያዩታል?

ከሌሎች ክለቦች አንጻር ክለባችን ከተመሰረተ አጭር ጊዜ ነው፡፡ ዋንጫ ማንሳታችን ብቻ ሳይሆን እንደ ክለብ በየአመቱ መሻሻል እየሳየን እንገኛለን፡፡ በዘንድሮው የውድድር ዘመንም የጥሎ ማለፉን ዋንጫ ማንሳት እና በአፍሪካ ውድድሮች ውስጥ መካፈል ቅዳችን ውስጥ ነበር፡፡ ይህንን አሳክተናል፤ በዚህም ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶናል፡፡ ለቀጣዮቹ ጊዜያትም የበለጠ እንድንሰራ ስንቅ የሚሆነን አንድ ታሪክ አስመዝግበናል፡፡ ለዚህ ስኬት ደግሞ አሰልጣኞች ፣ ተጫዋቾች ፣ አመራሮች እና በዙርያችን የሚገኙ ሁሉ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡

በቀጣዩ አመት (2018) የኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ትሳተፋላችሁ፡፡ ለዚህ ውድድር ብላችሁ እስካሁን የመጣችሁበትን አካሄድ ትቀይራላችሁ?

ሀገርን ወክሎ መሄድ የመጀመርያው ደረጃ ነው፡፡ ለዚህ የሚሆን ስብስብ ማዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡ ይህን ካደረግን እግረ መንገዳችንን በሊጉ እና ጥሎ ማለፉ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን ታሳቢ አድርገን ዝግጅታችንን የምናከናውን ይሆናል፡፡ ለዚህም በፋይናንስ በኩል ለመጠናከር ከወላይታ ልማት ማህበር በተጨማሪ የዞኑ አስተዳድር እና ሌሎች አካላት ተስፋ ሰጥተውናል፡፡

በወጪ ደረጃ ለወደፊቱም በተገቢው መንገድ ነው የምናወጣው፡፡ ለሚገባው ነገር ወጪ እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን አንድ ደረጃ ከፍ በማለታችን አመታዊ በጀታችንን መጨመራችን የማይቀር ነው፡፡

በፍጻሜው ያሸነፋችሁት መከላከያን ጨምሮ የሊጉ ክለቦች ከወላይታ ድቻ በብዙ እጥፍ ገንዘብ ያፈሳሉ፡፡ ነገር ግን በሜዳ ላይ ድቻ ከአብዛኛዎቹ ክለቦች የተሻለ ነው…

በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጥናት አድርጎ የክለቦችን አሰራር ተመልክቶ ከእኛ አሰራር ክለቦች ተሞክሮ እንዲወስዱ ማደረግ ቢችል መልካም ነው፡፡ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ከፍተኛ ገንዘብ በማፍሰስም ሆነ ዝቅተኛ ገንዘብ በማውጣት የሚገኘው ውጤት ተመሳሳይ ነው፡፡ ሁሉም ክለብ ራሱን መመልከት መጀመር አለበት፡፡ ገንዘብ ብቻውን ውጤታማ አያደርግም፡፡  ለብዙ ልማት የሚውል የሀገር ሐብት እንዲሁ እየባከነ ነው የሚገኘው፡፡ ስፖርት የልማት አካል አይደለም ማለቴ ሳይሆን በዘፈቀደ ሊባክን አይገባም፡፡ ባወጣነው መጠን ያገኘነውን እየለካን መሄድ ይኖርብናል፡፡ እኛ እንደ ክለብ ግብ እያስቀመጥን ነው የምሄደው ፤  ግባችን ላይ ለመድረስም ማውጣት የሚገባንን ወጪ በአግባቡ እናወጣለን፡፡ ስለዚህ እንደ ሀገር በእግርኳሱ ልንለወጥ የምንችለው ክለቦች ወደራሳችን መመልከት ስንጀምር ነው፡፡

በክለቡ የእስካሁን ጉዞ ላይ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ከፍተኛውን አስተዋፅኦ ይወስዳል፡፡ አሰልጣኝ መሳይ በክለባችሁ ያለው ቦታ ምንያህል ነው?

መሳይ በክለባችን ትልቅ ቦታ ነው ያለው፡፡ ክለቡ ሲመሰረት ጀምሮ እስካሁን አብሮን አለ፡፡ ለክለቡ ፣ ለሰዎች እንዲሁም ለስራው ታማኝ ነው፡፡ በሀገሪቱ የሚገኙ ትልልቅ አሰልጣኞች እንኳን ከአሰልጣኝ መሳይ ብዙ ሊማሩ የሚችሏቸው ነገሮች አሉ፡፡ ወደፊትም ትልቅ ደረጃ የመድረስ አቅም ያለው አሰልጣኝ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለመሳይ ጥንካሬ ሁልጊዜም ከጎኑ በመሆን የሚያግዘው የክለቡ ማኔጅመንት አስተዋጽኦ መጠቀስ ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የክለብ ኃላፊዎች በአሰልጣኞች ላይ የሚወስኗቸው ውሳኔዎች በስሜት የተሞሉ ናቸው፡፡ በእኛ በኩል ግን ለአንድ አሰልጣኝ ጊዜ መስጠት እና እቅዱን እንዲያሳካ ድጋፍ ማድረግ እንደሚኖርብን እናምናለን፡፡ በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት በአንድ ክለብ 8 አመት የቆየ አሰልጣኝ ቢኖር መሳይ ተፈሪ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *