ቻምፒየንስ ሊግ፡ የሰሜን አፍሪካ ክለቦች ሃያልነታቸውን ማሳየታቸውን ቀጥለዋል

በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሰሜን አፍሪካ ሃገራት ክለቦች አሁንም በአህጉሪቱ እግርኳስ ላይ ሃያል መሆናቸውን ማሳየታቸውን ቀጥለዋል፡፡ ከስምንቱ የሩብ ፍፃሜ ተፋላሚዎች ስደስቱ የሰሜን አፍሪካ ሃገራት ክለቦች ናቸው፡፡

ቅዳሜ ምሽት በተደረጉ ጨዋታዎችም ዋይዳድ ካዛብላንካ እና አል አሃሊ ከምድብ አራት ወደ ሩብ ፍፃሜው ማለፋቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ምድቡን ሲመራ የነበረው የዛምቢያው ዛናኮ በዋይዳድ ካዛብላንካ ተሸንፎ ከምድብ ተሰናብቷል፡፡ ካዛብላንካ ላይ በተደረገው ጨዋታ ዋይዳድ በመጀመሪያው 45 የጨዋታ የበላይ የነበረ ቢሆንም እንግዶቹ በተደጋጋሚ በመልሶ ማጥቃት የግብ እድሎችን ለመፍጠር ችለው ነበር፡፡ በሁለተኛው 45 በ57ኛው ደቂቃ ታዎንጋ ቡዌምባያ በሁለት ቢጫ ከሜዳ ሲሰናበት የዛናኮ ከኃላ የነበረው አይበገሬነትም ከድቶታል፡፡ ከፍተኛ ጫናን ማሳደር የቻሉት ዋይዳዶችም አሽራፍ ቤንሻሪጉ የ68ኛ ደቂቃ ግብ ወደ ቀጣይ ዙር ያለፉበትን ውጤት ማሳካት ችለዋል፡፡

አል አሃሊ ኮተን ስፖርትን አስተናግዶ ከምድቡ ሁለተኛ ሆኖ ያለፈበትን ውጤት ይዞ መውጣት ችሏል፡፡ 3-1 በተጠናቀቀው ጨዋታ የአህመድ ፋቲ የራስ ላይ ግብ የካሜሮኑን ክለብ በ12ኛው ደቂቃ ቀዳሚ ስታደርግ ከአሃሊ ጋር የመቀጠሉ ነገር አጠራጣሪ ነው የተባለለትን አጥቂው አምር ገማል ከርቀት መሬት ለመሬት የመታው ኳስ ግብ ሆኖ ሃያሉ የካይሮ ክለብ አቻ መሆን ችሏል፡፡ ሁለተኛ ግብ ለማከል ተጋጣሚያቸው ላይ ጫና የፈጠሩት አሃሊዎች በአብደላ ኤል ሰዒድ ግቡ የመጀመሪያውን አጋማሽ 2-1 መምራት ችለዋል፡፡ በሁለተኛው 45 ገማል የቡድኑን ሶስተኛ ለእራሱ ደግሞ ሁለተኛውን ግብ ቱኒዚያዊው ኢንተርናሽናል አሊ ማሎል ያሻገረውን የቅጣት ምት በግንባር በመግጨት አስቆጥሯል፡፡ አሃሊዎች ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት ያደረጉት ሳይሳካ ቢቀርም የዛናኮ በዋይዳድ መሸነፍ ተከትሎ የሉሳካውን ክለብ በግብ ክፍያ በመብለጥ ከ2013 ወዲህ ለመጀመሪያ ግዜ ከምድብ ማለፉን አረጋግጧል፡፡

ምድቡን ዋይዳድ ካዛብላንካ በ12 ነጥብ የምድቡ መሪ ሆኖ ሲያጠናቅቅ አል አሃሊ በ11 ነጥብ ዛናኮን በግብ ክፍያ በመብለጥ ሁለተኛ ሆኗል፡፡ ዛናኮ በተመሳሳይ 11 ነጥብ እንዲሁም ሁሉንም ጨዋታ የተሸነፈው ኮተን ስፖርት ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘው ውድድራቸውን ጨርሰዋል፡፡

ማሜሎዲ ሰንዳውንስ ከቪታ ክለብ ጋር 1 አቻ ሲለያዩ ቅዱስ ጊዮርጊስ በኤስፔራንስ 4-0 ተሸንፏል፡፡ ፕሪቶሪያ ላይ በተደረገው ጨዋታ ብራዚሎቹ በታቦ ንቴቴ ግብ ቀዳሚ ሲሆኑ ያዚድ አቶባ የኪንሻሳውን ክለብ በሁለተኛው አጋማሽ አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ ኤስፔራንስ በካሊል ቻማም፣ ቢለል ሜጅሪ፣ ሃይታም ጁኒ እና  አሊ ሜቻኒ ግቦች ቅዱስ ጊዮርጊስን 4-0 ረቷል፡፡ ውጤቱን ተከትሎ ኤስፔራንስ ምድብ ሶስትን በበላይነጥ አጠናቋል፡፡

ከምድብ ሁለት ዩኤስኤም አልጀር ካፕስ ዩናይትድ 4-1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ምድቡን በመሪነት ሲያጠናቅቅ የሊቢያው አል አሃሊ ትሪፖሊ ግብፅ ተጉዞ ከዛማሌክ ጋር ነጥብ መጋራቱን ተከትሎ ወደ ቀጣዩ ዙር ያለፈበትን ጣፋጭ ውጤት ማግኘት ችሏል፡፡ የእንግዶቹ የመከላከል ድክመት በታየበት ጨዋታ ዩኤስኤም አልጀር በዚሪ ሃማር እና ኦሳማ ዳርፋሎ ባስቆጠሯቸው ግቦች የአልጄሪያ መዲና ክለቡን ለድል አብቅተዋል፡፡ ለሃራሬው ክለብ ከባዶ ከመውጣት ያተረፈች ግብ አባስ አሚዱ በ81ኛው ደቂቃ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት አስቆጥሯል፡፡ በጨዋታው የአልጀርሱ ክለብ የተመሰረተበት 80ኛ አመት ዘክሯል፡፡

የ2016 የቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ተፋላሚ ዛማሌክ ከአል አሃሊ ትሪፖሊ ጋር 2-2 ተለያይቶ ከምድብ ተሰናብቷል፡፡ ባሰም ሞርሲ በግንባሩ በመግጨት የካይሮውን ሃያል መሪ ሲያደርግ አኒስ ሳልቶ የሊቢያ መዲናውን ክለብ በፍፁም ቅጣት ምት አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ዜግነት ያለው ቪያኒ ማቢዲ ያስቆጠራት ግሩም ግብ አሃሊ ትሪፖሊን 2-1 እንዲመራ ብታስችልም ናይጄሪያዊው ማሩፍ የሱፍ ዛማሌክን ዳግም አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ የምድብ ጨዋታዎቹን በገለልተኛ ሜዳ ቱኒዚያ እና ግብፅ ላይ ሲያደርግ ለነበረው አሃሊ ትሪፖሊ ውጤቱ የማይታመን ሆኗል፡፡ ክለቡ በውጣ ውረዶች ውስጥም ሆኖ ሩብ ፍፃሜ መግባት ችሏል፡፡ ምድቡን ዩኤስኤም አልጀር በ11 ነጥብ በቀዳሚነት ሲጨርስ አል አሃሊ ትሪፖሊ በ9 ነጥብ ሁለተኛ ሆኗል፡፡ ዛማሌክ እና ካፕስ ዩናይትድ በእኩል 6 ነጥብ ተከታዮቹን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡

 

 

ወደ ሩብ ፍፃሜ ማለፋቸውን ያረጋገጡ ክለቦች (ጨዋታዎቹ ጳጉሜን 3 ይጀምራሉ)

ኤትዋል ስፖርቲቭ ደ ሳህል (ቱኒዚያ)፣ ፌሮቫያሪዮ ደ ቤይራ (ሞዛምቢክ)፣ ኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝ (ቱኒዚያ)፣ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (ደቡብ አፍሪካ)፣ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ (ሞሮኮ)፣ አል አሃሊ ትሪፖሊ (ሊቢያ)፣ ዩኤስኤም አልጀር (አልጄሪያ) እና አል አሃሊ (ግብፅ)

 

የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች

ኤትዋል ደ ሳህል ከ አል አሃሊ ትሪፖሊ

ዩኤስኤም አልጀር ከ ፌሮቫያሪዮ ቤይራ

ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ ከ አል አሃሊ

ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ ከ ማሜሎዲ ሰንዳውንስ

 

የቅዳሜ ውጤቶች

ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ 1-0 ዛናኮ

አል አሃሊ 3-1 ኮተን ስፖርት

 

የእሁድ ጨዋታ

ኤስፔራንስ ስፖርቲቭ ደ ቱኒዝ 3-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ማሜሎዲ ሰንዳውንስ 1-1 ኤኤስ ቪታ ክለብ

ዩኤስኤም አልጀር 4-1 ካፕስ ዩናይትድ

ዛማሌክ 2-2 አል አሃሊ ትሪፖሊ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *