ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና አቻ ተለያይቶ ወደ መለያ ጨዋታው አምርቷል

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ 30ኛ ሳምንት ሲጠበቁ ከነበሩት ጨዋታዎች አንዱ የነበረው የሀዲያ ሆሳዕና እና ሀላባ ከተማ ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተፈጽሟል፡፡ 

በአቢዮ አርሳሞ መታሰቢያ ስታድየም ቁጥሩ እጅግ በርካታ የሀዲያ ደጋፊዎችና ቁጥሩ ቀላል የማይባል የሀላባ ከነማ ደጋፊዎች የታደሙበት ጨዋታ አስደሳች የደጋፊዎች ድባብ ተመልክተንበታል፡፡

ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ 90 በጥሩ ብቃት በመሩት ጨዋታ ሀላባ ከተማዎች በአምበላቸው አበባው አመኑ አማካኝነት የሀድያው ሆሳዕናው አምበል ኄኖክ አርፊጮ ሀድያ ከ ደቡብ ፖሊስ ጋር ባደረጉት ጨዋታ በተመለከተው የቀይ ካርድ ምክንያት የ4 ጨዋታ ቅጣቱን ሳይጨርስ በዚህ ጨዋታ ውስጥ  መሰለፍ አይገባውም በማለት ክስ በማዝያዝ የጀመረ ሲሆን ባለሜዳዎቹ ሀድያዎች ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን በሁሉም መልኩ ተሽለው ቀርበዋል፡፡ በተለይ በ37ኛው ደቂቃ በበረከት ወ/ዮሐንስ እና እንዳለ ደባልቄ አማካኝነት ከማዕዘን በተሻገሩ ኳሶች ግልፅ የማግባት አጋጣሚ አግኝተው ሳይጠቀሙ ቀሩ እንጂ ሀድያ ሆሳዕና ጎል አስቆጥረው እረፍት በወጡ ነበር ።

በአንፃሩ ሀላባዎች በጥብቅ መከላከል ተጠምደው የዋሉ ሲሆን በመጀመርያው አጋማሽ የሚጠቀስ የጎል ማስቆጠር አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ቀርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ በጨዋታው ላይ የሚያስፈልጋቸውን ውጤት ለማግኘት ገና በ20 ደቂቃ ውስጥ ሁለቱም ቡድኖች ሦስት ቅያሪያቸውን ሲጠቀሙ ጎል ለማስቆጠር በሚያደርጉት ጥረት እንደ መጀመርያው አጋማሽ ሀድያዎች የተሻሉ ነበር። በተለይ ከማዕዘን በሚሻገሩ ኳሶች የፈጠሯቸው የግብ አጋጣሚዎች በግቡ አግዳሚ እና በጠንካራዎቹ የሀላባ ተከለካዮች ጥረት ጎል ሳይቆጠር ቀርቷል፡፡

ወደ ጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ የአቻ ውጤቱን የፈለጉት የሚመስሉት ሀድያዎች ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸውን ተከትሎ ማጥቃት የጀመሩት ሀላባዎች በጨዋታው የመጀመርያ የጎል ሙከራቸውን በበአቦነህ ገነቱ ቢሞክሩም ግብ ጠባቂው አስራት ሚሻሞ አድኖበታል፡፡ ከደቂቃ በኋላ ደግሞ የከፍተኛ ሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እየመራ የሚገኘው ዘካርያስ ፍቅሬ ግልፅ የሆነ የጎል አጋጣሚ አግኝቶ ያመከናት ኳስ የምታስቆጭ ነበረች። ጨዋታውም ያለ ግብ በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ ጅማ ከተማ ወልቂጤ ከተማን 3-1 በማሸነፉ በ56 ነጥቦች በቀጥታ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ ሀድያ ሆሳህና በ54 ነጥቦች ሁለተኛ ሆኖ በማጠናቀቅ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ ሐምሌ 11 ቀን 2009 በ08:00 ድሬዳዋ ላይ ከመቀለ ከተማ ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ለመጠበቅ ተገዷል ።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ዻውሎስ ጌታቸው – ሀዲያ ሆሳዕና

ጨዋታውን አሸንፈን መውጣት ይገባን ነበር። ሆኖም ተጫዋቾቼ ጎል ለማስቆጠር ከነበራቸው ጉጉት የተነሳ ብዙ ጎሎችን አምክነዋል፡፡ ያ ደግሞ የጅማ ከተማን ውጤት እየሰሙ መሆኑ በራሱ ተፅዕኖ ነበረው።  ያም ቢሆን በተጫዋቾቼ ደስተኛ ነኝ። ጊዜው ረዘመ እንጂ  ድሬደዋ ላይ መቀለን አሸንፈን ፕሪምየር ሊግ እንደምንገባ እርግጠኛ ነኝ፡፡

አሰልጣኝ ሚሊዮን አካሉ – ሀላባ ከተማ

ጨዋታው በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ሆኖም የሜዳው አለመመቸት የፈለግነውን የጨዋታ እንቅስቃሴ እንዳናደርግ ገድቦናል፡፡ ሊጉ እጅግ አስቸጋሪ ፣ፈታኝ እና አድካሚ ነው፡፡ በቀጣይ ጠንክረን እንቀርባለን፡፡

በመጨረሻም

ጨዋታውን ለመከታተል የፕሪሚየር ሊጉ አሰልጣኞች የሆኑት የወላይታ ድቻው መሳይ ተፈሪ ፣ የድሬደዋው ዘላለም ሽፈራው እንዲሁም የጅማ አባቡናው አሰልጣኝ ገ/መድህን ሀይሌ በስታድየሙ በመገኘት ጨዋታውን ሲከታተሉ እንደነበረ ለማየት ችለናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *