ሪፖርት | ጅማ ከተማ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊግ አድጓል

የ30ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ወሳኝ ጨዋታዎች ዛሬ ሲደረጉ ጅማ ላይ ወልቂጤ ከተማን ያስተናገደው ጅማ ከተማ 3-1 በሆነ ውጤት አሸንፎ በ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ መሳተፉን አረጋግጧል፡፡

የጅማ ስታድየም በተመልካች ተሞልቶ ጨዋታው የተካሄደ ሲሆን ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ የወልቂጤ ደጋፊዎችም በስፍራው ተገኝተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያደረጉት ጨዋታ የጨዋታውን ውጤት ባልተገባ መንገድ የመወሰን ተግባር ተፈጽሟል በሚል የሀዋሳ ከተማ ክለብ ፕሬዝዳንት መናገራቸውን ተከትሎም በዛሬው እለት በስታድየሙ ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸው መልዕክቶች የሚያስተላልፉ በርካታ ባነሮች መታየታቸው በጨዋታው ከተከሰቱ ነገሮች አንዱ ነው፡፡

ኢንተርናሽናል የመሀል ዳኛ ሃይለየሱስ ባዘዘው በመሩት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ጅማ ከተማ ወደ ጎል በመድረስ ረገድ የተሻሉ ቢመስሉም የጠራ የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ግን መፍጠር አልቻሉም ነበር፡፡ በአንድ የፊት አጥቂ ወደ ሜዳ የገቡት ወልቂጤ ከተማዎች ከነበረባቸው የሜዳ ላይ ጫና አንፃር ተከላክለው ለመጫወት ሲሞክሩ ተስተውሏል፡፡

በ36ኛው ደቂቃ ከማዕዘን የተሻገረውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ኄኖክ መሃሪ ጅማ ከተማን መሪ ማድረግ ቢችልም ከጎሉ መቆጠር በኃላ ጨዋታው ለ20  ደቂቃዎች ተቋርጦ ነበር፡፡ ከጨዋታው በፊት በተለምዶ ካታንጋ በሚባለው የደጋፊዎች መቀመጫ አካባቢ በነበሩ የወልቂጤ እና የጅማ ከተማ ደጋፊዎች መካከል የሚለይ ምንም አይነት የፖሊስ ሃይልም ሆነ አጥር ባለመኖሩ ቅሬታቸውን ሲያነሱ የነበሩት ወልቂጤ ከተማዎች ከጎሉ መቆጠር በኃላ በዚሁ ምክንያት የሁለቱ ቡድን ደጋፊዎች መካከል ግጭቶች ተነስተው ነበር፡፡ በግጭቱ ከወልቂጤ ከተማ በኩል አንድ እንስት እንዲሁም ግርግሩን ለማብረድ ሲጥር በነበረ አንድ የፀጥታ አስከባሪ ላይ መለስተኛ ጉዳቶች ተከስተዋል፡፡ ግርግሩን ለማብረድ የወልቂጤ ከተማ ተጨዋቾች ጥረት ሲያደርጉም ተስተውለዋል፡፡

ጨዋታው ከ20 ደቂቃዎች መቋረጥ በኃላ ሲቀጥል በመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ጅማ ከተማዎች ተጨማሪ ጎሎችን ለማስቆጠር ጥረት ቢያደርጉም የመጀመሪያው አጋማሽ ግን ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር 1-0 በሆነ ውጤት ነበር የተጠናቀቀው፡፡

ከዕረፍት መልስ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወልቂጤ ከተማዎች መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን ጅማ ከተማዎች በ48ኛው ደቂቃ በኄኖክ መሃሪ አማካኝነት መሪነታቸውን ወደ ሁለት ከፍ ማድረግ ችለዋል፡፡ ወልቂጤ ከተማዎች በተቃራኒው ሙሉ ለሙሉ አጥቅተው ለመጫወት ቢሞክሩም ሳይሳካላቸው ቀርተዋል፡፡ የጅማ ከተማዎችን የመጨረሻም ጎል አቅሌሲያ ግርማ በ55ኛው ደቂቃ ግብ ጠባቂውን አልፎ ማስቆጠር ችሏል፡፡

ሶስት ጎሎችን ካስቆጠሩ በኃላ ተጠንቅቀው ለመጫወት ሲጥሩ የነበሩት ጅማ ከተማዎች ተረጋግተው በራሳቸው ሜዳ ላይ ኳሶችን ለማንሸራሸር እና ከወልቂጤ ከተማ በኩል የሚመጣውን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለመገደብ ሲሞክሩ ተስተውለዋል፡፡ ወልቂጤ ከተማን ከመሸነፍ ያላዳነችውን ኳስ አክሊሉ ተፈሪ በ89ኛው ደቂቃ ማስቆጠር የቻለ ቢሆንም ከደቂቃው አንፃር ወልቂጤ ከተማዎች ተጨማሪ የጎል ሙከራዎችን ሳያደርጉ ጨዋታው በጅማ ከተማ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ውጤቱን ተከትሎ በ1973 የተመሰረተው ጅማ ከተማ በ56 ነጥቦች ምድቡን በበላይነት በማጠናቀቅ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን አረጋግጧል፡፡

5 Comments

  1. ግልጽ ደብዳቤ ለኢትዮጵያ foot ball federation
    ”break the silence” ዝምታው ይሰበር እንጂ የኢትዮጵያ foot ball federation where is the justice ?????
    የጨዋታ ውጤት በሙስና በሚያስቀይሩ (በ match fixing ) ክለቦች ላይ በፊፋም ሆነ በኢትዮጵያ foot ball federation ህጎች ላይ የተደነገገውን ለመተግበርና እርምጃ ለመውሰድ ምኑ ነው ያስቸገራችሁ????? ለዚያውም በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ያደረጉት ጨዋታ የጨዋታውን ውጤት ባልተገባ መንገድ የመወሰን ተግባር ተፈጽሟል በሚል የሀዋሳ ከተማ ክለብ ፕሬዝዳንት መናገራቸውን በተጨበባጭ ማስረጃ እየተረጋገጠ? በዚህ አጋጣሚ የሀዋሳ ከተማ ክለብ ፕሬዝዳንት ሙስናን በመጸየፍ ለፈጸሙት አኩሪ ታሪክ በአርዐያነታቸው እጅግ እያመሰገንኳቸው ፌዴሬሽኑና መንግስትም ተግባራቸውን ለአስተማሪነት በመጠቀመም ማበረታቻና የእውቅና ሽልማት ቢሰጣቸው

  2. እድሜ ለሙሰኛዉ እና ወራዳዉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን አስራ አንድ ደረጃዎችን አሽቆልቁለናል ገና መቶ ደረጃ ይቀረናል ወራዳ ባለጌ ትዉልድ ገዳይ ፌደሬሽን እነዚህ ሚገዛ ካገኙ ሀገር ከመሸጥ ወደ ኻላ አይሉም

  3. ALHAMDLILLAH be jimma city dil tedestenal. Soccer ethiopiawoch ibakachihun ye ethio electric asafari yemusna tegbar post litaregu yigebal. Ye hawassa city club president beyifa asafari yemusna tegbar mekahedun iyetenageru inante zm atbelu inji.

Leave a Reply