ሪፖርት | ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ሲያድግ መቀለ ወደ መለያ ጨዋታው አምርቷል 

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ 30ኛ ሳምንት ወደ መቀለ ያመራው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ  1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቶ ወደ 2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን አረጋግጧል፡፡ ትራንስ ኢትዮጵያ በ2003 የውድድር ዘመን ከሊጉ ከተሰናበተ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ የትግራይ ክለብ ወደ ሊጉ ማደግም ችሏል፡፡

ከጨዋታው በፊት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ምድቡን በ63 ነጥብ እና 33 የግብ ልዩነት እንዲሁም መቀለ ከተማ በ60 ነጥብ እና 21 የግብ ልዩነት በሁለተኛ ደረጃ ላይ በመቀመጣቸው መቀለ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ ጨዋታውን ከ6-0 በላይ በሆነ ውጤት የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ነበር፡፡

ከቀኑ 6 ሰአት ጀምሮ እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው የሁለቱ ክለቦች ደጋፊዎች መሞላት የጀመረው የመቀለ አለምአቀፍ ስታድየም የጨዋታ መጀመር አንድ ሰአት በፊት ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል መልኩ ሞልቶ ጨዋታውን አስተናግዷል፡፡ ከጨዋታው መጀመር በፊት ከሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች የተወከሉ ደጋፊዎች በስታዲየሙ ውስጥ እየተዘዋወሩ የክልሉን ባህል የሚያንፀባርቅና የክለቦቹን ወዳጅነት የሚያሳይ ትርኢትንም አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ተክለወይኒ እንዲሁም አቶ አበበ ገላጋይ የሁለቱን ቡድኖች ተጫዋቾች ከተዋወቁ በኃላ የክልሉ ባህላዊ ምግብ የሆነውን ጥህሎ ከሁለቱ ቡድኖች አምበሎች ጋር በመቅመስ ጨዋታውን አስጀምረዋል፡፡

በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ከፍተኛ የመሸናነፍ ፉክክርና እልህ የተሞላበት ጨዋታ ነበር፡፡ ሆኖም በመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች በመሀል ላይ ቶሎ ቶሎ ከሚቆራረጡ ቅብብሎች በዘለለ ይህ ነው የሚባሉ የጠሩ የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡

በዚሁ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወደ ግብ የተደረጉት ሙከራዎች በአመዛኙ ከሳጥን ውጪ በቀጥታ የሚመቱ ኳሶች ነበሩ፡፡ መቀለ ከተማዎች በአጥቂዎቻቸው ያሬድ ከበደ እና አማኑኤል ገ/ሚካኤል በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል፡፡ በአንጻሩ ወልዋሎዎች በውሰት ከደደቢት ቡድኑን የተቀላቀለው ብርሃኑ አሻሞና መኩሪያ ደሱ ከርቀት አክርረው ወደ ግብ ሞክረው ሶፎንያስ ሰይፈ ካዳነባቸው ኳሶች ውጪ የሚጠቀስ የግብ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም፡፡

በአመዛኙ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ በታየበት በዚሁ ጨዋታ ከተደረጉት ሙከራዎች መካከል በ33ኛው ደቂቃ አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከግራ መስመር ያሳለፈለትን ኳስ ያሬድ ከበደ ከበረኛው ጋር ተገናኝቶ ሳይጠቀምበት የቀረው ኳስ በጣም አስቆጪ ነበር፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ መቀለ ከተማዎች ጨዋታውን አሸንፈው ለመውጣት ከፍተኛ ተነሳሽነትን በማሳየት የጨዋታውን የበላይነት ወስደው መጫወት ችለዋል፡፡ በ56ኛው ደቂቃ ላይ አስራት ሸገሬ ሞክሯት በረከት ያዳነበት እንዲሁም በ59ኛው ደቂቃ ያሬድ ከበደ ያመከናት ፍፁም ግልጽ የግንባር ኳስም ለግብነት የቀረቡ እድሎች ነበሩ፡፡

 

ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ይበልጥ ጫና መፍጠር የቻሉት መቀለዎች በ64ኛው ደቂቃ የውድድር ዘመኑ አጋማሽ ላይ ከኢትዮጵያ መድን ቡድኑን የተቀላቀለው አስራት ሸገሬ ግብ አስቆጥሮ የመቀሌ ደጋፊዎችን ማነቃቃት ችሎ ነበር፡፡ ከግቧ መቆጠር በኃላ በደቂቃዎች ልዮነት መቀለዎች ልዩነታቸውን ወደ ሁለት ሊያሰፉበት የሚችሉበትን ወርቃማ እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

ጨዋታው  በመቀለ ከተማ የ1-0 አሸናፊነት ተጠናቀቀ ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት በ90+3ኛው ደቂቃ ላይ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ሳምሶን ተካን ቀይሮ የገባው የቀድሞው የደደቢት ተጫዋች አለምአንተ ካሳ ወልዋሎዎች በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን አጋጣሚ ከመቀሌ የግብ ክልል ጠርዝ ላይ በቀጥታ በመምታት ግሩም ግብን አስቆጥሮ ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡

በ1948 የተመሰረተውና በ1970ዎቹ  ፣ 80ዎቹ እና 90ዎቹ በተደጋጋሚ የመፍረስ አደጋ አጋጥሞት በ2004 እንደአዲስ የተመሰረተው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ2003 የውድድር ዘመን መጨረሻ ከኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተሰናበተው ትራንስ ኢትዮጵያ እና በ2000 የወሰደወ ጉና ንግድን ተከትሎ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚካፈል 3ኛው የትግራይ ክለብ ሆኗል፡፡

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ አንዳንድ የመቀለ ከተማ ደጋፊዎች በፈጠሩት ግርግር የወልዋሎ የቡድን አውቶብስ ላይ ጉዳት ደርሷል

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *