“እኛ ያለ ደጋፊዎቻችን ጥርስ የሌለው አንበሳ ነን” አሰልጣኝ ብርሀኔ ገብረእግዚአብሔር

በ2009 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ አመዛኙን የውድድር ዘመን የሰንጠረዡ አናት ላይ በመቀመጥ ጥንካሬውን ያሳየው ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ማደጉን አረጋግጧል፡፡ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያሳለፈው አሰልጣኝ ብርሃኔ ገ/እግዚአብሔር ቡድኑ ስላሳለፈው የውድድር ዘመን እንዲሁም ስለክለቡ አጠቃላይ ሁኔታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም እንደ ኢትዮጵያ መድን ፣ ደመራ ፣ ኪራይ ቤቶች የመሳሰሉ ክለቦችን ወደ ዋናው ሊግ (ከዚህ ቀደም በነበረው 1ኛ ዲቪዝዮን) አሳድገሃል፡፡ አሁን ደግሞ ወልዋሎን በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ለፕሪምየር ሊግ አብቅተኸዋል፡፡ የዚህ ታሪክ ዋነኛ ተጠቃሽ ከሆንክ በኃላ ምን ተሰማህ?

እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡ አይደለም እንደዚህ አይነት ድሎችን አስመዝግበህ እንዲሁ አንድ ጨዋታ ስታሸንፍ ራሱ በጣም ትደሰታለህ፡፡ ነገር ግን ጨዋታዎችን እያሸነፍክ ስትሄድ ከፊትህ ሌላ ከባባድ ፈተናዎች ናቸው የሚገጥሙህ፡፡ ግዴታ እነዛን ከባድ ፈተናዎች ለማለፍ ደግሞ ዝግጁ መሆን አለብህ፡፡ ሌላ ደስታ ለማምጣት ለዛ ደግሞ ጠንክረህ መስራት አለብህ፡፡ ሁልጊዜ አሸናፊ ቡድን ሃላፊነቱ እየበዛ ስለሚሄድ ከደስታዬ እኩል የወደፊቱንም ነገው እያሰብኩ ነው ያለሁት፡፡

የ2009 ዓም የከፍተኛ ሊግ ውድድር በአንተ እይታ ምን መልክ ነበረው?

ውድድሩ በጣም ውጥረት የነበረበት ውድድር ነው፡፡ ሁሉም ክለቦች ጠንካራ ነበሩ ፤ እኛ እንኳን ማለፋችንን ያረጋገጥነው በመጨረሻ ጨዋታ ነው፡፡ እዛኛው ምድብም ሁላችሁም እንደተመለከታችሁት እስከ መጨረሻኛ ሳምንት ጨዋታዎች ድረስ የሚያልፈው ቡድን አልታወቀም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ የሚያሳየው ውድድሩ ምን ያህል ፈታኝ እንደነበረ ነው፡፡

በአብዛኛውን የውድድር ዘመን የሰንጠረዡ አናት ላይ ተቀምጣችሁ ስኬታማ የውድድር ዘመን አሳልፋችኃል….

መጀመሪያ ላይ አንድ ቡድን ሲነሳ እቅዶች ሊኖሩት ይገባል፡፡ እኛም ያንን ነው ያደረግነው፡፡ እቅዶቻችንን አስቀመጥን በእቅዳቻችን መሰረት ዝግጅታችንን አጠናክረን አደረግን፡፡ ዋነኛ እቅዳችን የነበረው በአማካይ ከሁለት ጨዋታ አራት ነጥቦችን ለመያዝ ነበር ይህን ስታስበው የምንጫወተው 30 ጨዋታዎች እንደመሆኑ በአጠቃላይ 60 ነጥቦችን ለመሰብሰብ ነበር፡፡ ከፈጣሪ ጋር ከእቅዳችን በላይ 64 ነጥቦችን ሰብስበን ወደ ሊጉ መጥተናል፡፡ ሌላው እኔ ቡድኑን ስረከበው ከነበሩት ተጨዋቾች ጋር አዳዲስ ወጣት ተጨዋቾችን ቀላቅዬ ጥሩ ቡድን ለመስራት ሞክሬአለሁ ግን ዋነኛ የቡድኔን ቅርፅ የሰራሁት መጀመሪያ የውድድር ዘመኑ ሳይጀመር በዝግጅት ወቅት ነበር፡፡ ያም ነው ለዚህ ያበቃኝ፡፡

የክለቡ አመራሮችስ ከቡድኑ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እንዴት ነበር?

የሚገርመው የወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ የክለብ አመራሮች ከሌሎች የክለብ አመራሮች የሚለዩት እግር ኳስ ተጫውተው ያለፉ መሆናቸው ነው፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ለክለቡ ለራሱ የተጫወቱ ናቸው፡፡ ስለዚህ የኔነት ስሜት ከሚገባው በላይ ይሰማቸው ነበር ፤ ይህ ደግሞ ለአንድ ቡድን እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ ሁልጊዜ ስንገናኝ የምናወራው ስለ እግርኳስ ነው፡፡ ስለ ክለቡ ራሱ ለማውራት ስብሰባ ተጠራርተን አናውቅም፡፡ ምክንያቱም ሁልጊዜ ወይ ከክለቡ ስራ አስፈፃሚ ወይም ከቦርድ አመራሮች አልያም ከቴክኒካል ሃላፊዎች ጋር በየልምምዱ ስለምንገናኝ በየጊዜው አዳዲስ ነገሮች ላይ እንወያያለን፡፡ እነሱም ወርደው እኛን በቅርበት ስለሚመለከቱን ግንኙነታችን የጠበቀ ነበር፡፡ በዚህ መንገድ ለሌሎች ክለቦች ሞዴል መሆን እንችላለን፡፡

ለቡድኑ ውጤታማነት የደጋፊዎቻችሁ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር፡፡ ስለ ደጋፊዎቻችሁ ምን ትላለህ?

የደጋፊዎች የአደጋገፍ መንገድ ላይ ብዙ ስራዎችን ሰርተናል፡፡ ሁሉም ደጋፊ ለብጥብጦች ጥፋተኛ ናቸው ማለት አትችልም፡፡ በአንዳንድ ደጋፊዎች ጥፋት ሁሉንም መውቀስ አትችልም፡፡ ማድረግ ያለብህ እነዛን ሰዎች ማስተማር ነው፡፡ ስለዚህ በዋነኝነት ሚድያን በመጠቀም እዛው በአካባቢያችን ባሉ የብዙሃን መገናኛዎች መልክቶችን በማስተላለፍ እንደነዚህ አይነት አገሮችን ለማጥፋት ሞክረናል፡፡ በአጠቃላይ ግን የቡድናችን ደጋፊዎች በጣም የሚያስገርሙ ነበሩ፡፡ ቡድኑን እንደ 12ኛ ተጫዋች የምር ሲደግፉት ነበር፡፡ እኛ እንደውም ያለ ደጋፊዎቻችን ጥርስ የሌለው አንበሳ ነበርን፡፡

በቀጣይ ከቡድን ግንባታ ጋር በተያያዘ ምን አዳዲስ ነገሮች ይኖራሉ? ያንተስ ከቡድኑ ጋር ያለህ ቆይታ ተረጋግጧል?

እኔ በግሌ በዚህኛው አመት ከክለቡ ጋር ያለኝ ኮንትራት አብቅቷል፡፡ ነገር ግን በኔም በክለቡ ከፍተኛ አመራሮች በኩል ያለው አስተሳሰብ በቀጣይ ከክለቡ ጋር እንደምቆይ ነው፡፡ በርግጠኝነት ግን ከፊታችን ካለው የአሸናፊዎች አሸናፊ ጨዋታ በኃላ ሁለታችንም ቁጭ ብለን ያለውን ነገር ለማጥራት እንሞክራለን፡፡ ቡድኑን በተመለከተ ቡድን አፍርሼ ሌላ ቡድን አልገነባም፡፡ አሁን ጥሩ አሸናፊ ቡድን አለኝ፡፡ ይህንን ቡድን ባሉኝ የመዘጋጃ ጊዜያት ማጠናከር ነው ያለብኝ፡፡ባሉብን ክፍተቶች ላይ በደንብ በመስራት በሊጉ ላይ በጥሩ መልኩ ለመቅረብ እንሞክራለን፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *