የኢትዮዽያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የሚካሄድባቸው ቀናት ታወቁ

የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ እና የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ አሸናፊዎች የሚያደርጉት የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ (ሱፐር ካፕ) ጨዋታዎች “በደርሶ መልስ” መስከረም 2010 ላይ እንደሚደረጉ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን መርሀ ግብር ያሳያል፡፡

በሊጉ አሸናፊ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና በጥሎ ማለፉ ባለ ድል ወላይታ ድቻ መካከል የሚደረገው ጨዋታ በደርሶ መልስ መልክ የሚደረግ ቢሆንም ሁለቱም ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ስታድየም የሚደረጉ ይሆናል፡፡ ሶከር ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙርያ ከፌዴሬሽኑ ባገኘችው መረጃ በውድድሩ ደንብ አንቀፅ 3 መሰረት የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ በደርሶ መልስ ( በሁለት ጨዋታ )  አዲስ አበባ ላይ ይካሄዳል የሚል ደንብ በመኖሩ የውድድሩ አሸናፊ የሚለየው በሁለት ጨዋታ በሚዘገበው ውጤት መሰረት ይሆናል። በዚህም መሰረት በመጀመርያው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ባለ ሜዳ የሚሆን ሲሆን በሁለተኛው ጨዋታ ወላይታ ድቻ ባለሜዳ ይሆናል፡፡ የውጤት አመዘጋገቡም በደርሶ መልስ ህጎች መሰረት ይሆናል፡፡

ውድድሩ በአንዳድ ወቅቶች አዲስ አበባ ላይ በተደረጉ የደርሶ መልስ ጨዋታዎች የተካሄዱ ሲሆን በ2000 ቅዱስ ጊዮርጊስ በደርሶ መልስ 5-4 ድምር ውጤት ኢትዮጵያ ቡናን አሸንፎ ካነሳበት ውድድር በኋላ በደርሶ መልስ ተካሂዶ አያውቅም፡፡ ውድድሩ ለመጨረሻ ጊዜ የተካሄደው በ2007 አሸናፊዎች መካከል ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በመለያ ምቶች መከላከያን አሸንፎ ማንሳቱ የሚታወስ ነው፡፡

*የመጀመርያ ጨዋታ

ሀሙስ መስከረም 25 ቀን 2010

10:00 ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ

*ሁለተኛ ጨዋታ

እሁድ መሰከረም 28 ቀን 2010

10:00 ወላይታ ድቻ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

በ1977 የተጀመረው ይህ ውድድር ለ25 ጊዜያት ሲካሄድ ቅዱስ ጊዮርጊስ 15 ጊዜ ዋንጫውነን በማንሳት ቀዳሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡና 5 ፣ ኤሌክትሪክ 3 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ይከተላሉ፡፡

ውድድሩ በተለያዩ ምክንያቶች ለ10 ጊዜያት ያህል መካሄድ ያልቻለ ሲሆን በመንግስት ለውጥ ወቅት (በ1983 እና 1984) ፣ አንድ ክለብ ሁለቱንም ዋንጫ በማሸነፉ ምክንያት ( 1991፣ 1993 ፣ 2001 እና 2008) በክለቦች እና ፌዴሬሽኑ ውዝግብ (1999) ያልተካሄዱ አመታት ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ  በ2004 ፣ 2005 እና 2006 በጊዜ መጣበብ እና ሌሎች ያልታወቁ ምክንያቶች የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *