የክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ሐምሌ 5 በይፋ የተከፈተ ሲሆን በርካታ ተጫዋቾችም ዝውውር እየፈጸሙ ይገኛሉ፡፡ በዚህ ጥንቅር ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የተያያዙ የዝውውር ወሬዎችን ተመልክተናል፡፡
ለክለቡ የፈረሙ
ጥላሁን ወልዴ
የተጠናቀቀው የውድድር ዘመንን በሁለት ክለቦች ያሳለፈው ጥላሁን ወልዴ ወደ ኤሌክትሪክ ማምራቱ የተረጋገጠ ተጫዋች ነው፡፡ ቡናን ለቆ ወደ አዳማ ከተማ ከተዛወረ በኋላ በውድድር ዘመኙ አጋማሽ ንግድ ባንክን የተቀላቀለው ጥላሁን ከሊጉ በወረደው ክለብ የተሻለ የመሰለፍ እድል ማግኘት ችሏል፡፡
ዮሀንስ በዛብህ
ከሀዋሳ ከተማ በተጠናቀቀው የውድድድ አመት ኢትዮጵያ ቡናን የተቀላቀለው ዮሀንስ በዛብህ በቡና ጥቂት ጨዋታዎችን አድርጎ ክለቡን በመልቀቅ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ተቀላቅሏል፡፡
ውላቸውን ያደሱ ተጫዋቾች
በክለቡ ረጅም ጊዜ የቆዩት አዲስ ነጋሽ እና አወት ገብረሚካኤል ውላቸውን ለተጨማሪ ሁለት አመታት ሲያድሱ ከወላይታ ድቻ ተዛውሮ ሁለት የውድድር ዘመናት ያሳለፈው ተከላካዩ ተስፋዬ መላኩ እና ከተስፋ ቡድኑ ያደገው አማካዩ በኃይሉ ተሻገር ውላቸውን ለተጨማሪ ሁለት አመታት ያራዘሙ ሌሎች ተጫዋቾች ናቸው፡፡
ከክለቡ ጋር ስማቸው የተያያዙ ተጫዋቾች
ኄኖክ አዱኛ ለክለቡ ለመፈረም ተስማምቶ እንደነበር ቢነገርም በቦታው የሚጫወተው አወት ገብረሚካኤል ውሉን ማራዘሙን ተከትሎ ኤሌክትሪክን የመቀላቀሉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ውሉ የተጠናቀቀው ምንያህል ተሾመ ወደ ኤሌክትሪክ ሊዛወሩ ከሚችሉ ተጫዋቾች መካከል ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ሲሆን የአርባምንጮ ከተማዎቹ አመለ ሚልኪያስ እና ታደለ መንገሻ ፣ ከአዳማ ከተማ እንደለቀቀ የታወቀው ኄኖክ ካሳሁን እንዲሁም የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ግርማ በቀለ በቀይ እና ነጭ ለባሾቹ ከሚፈለጉ ተጫዋቾች መካከል ናቸው፡፡
የለቀቁ / ሊለቁ የሚችሉ ተጫዋቾች
ከክለቡ መልቀቁ የተረጋገጠው ተጫዋች አሳልፈው መኮንን ብቻ ነው፡፡ ዘንድሮ በጉዳት አመዛኙን የጨዋታ ጊዜ ያሳለፈው አሳልፈው መኮንን ወላይታ ድቻን ተቀላቅሏል፡፡ ኮንትራታቸው የተጠናቀቀው ኢብራሂም ፎፋና ፣ አሸናፊ ሽብሩ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ከክለቡ ሊለቁ የሚችሉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡