ሁለተኛው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ቤተሰብ የሩጫ ውድድርና ክለቡ ለሚያስነባው ከ35እስከ 40ሺህ ሰዎችን የማስተናገድ አቅም እንደሚኖረው የሚጠበቀው ስታዲየም የመሠረት ድንጋይ የማስቀመጥ ስነስርዓት የክለቡ ከፍተኛ አመራሮች ፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም የክለቡ ደጋፊዎች በተገኙበት ዛሬ ረፋድ በለቡ ተካሄዷል፡፡
ከ10ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የተሳተፉበትን 2ኛው የኢትዮጵያ ቡና ስፓርት ክለብ የቤተሰብ ሩጫ ውድድር በክብር እንግድነት ተገኝተው ያስጀመሩት ጀግናዋ አትሌት ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዘዳንት የሆኑት አቶ ጁነዲን በሻ ከክለቡ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመሆን በጋራ ውድድሩን አስጀምረዋል፡፡
በ2007 ጅማሮውን ያደረገው ይህ ሩጫ በ2008 ሳይካሄድ ቀርቶ ዘንድሮ ዳግም ሲካሄድ ከመጀመሪያው ውድድር መጠነኛ የቦታ ለውጦች ተደርገውበት ነበር በዚህም መሠረት በዛሬው ውድድር የውድድሩ መጨረሻ የነበረው የክለቡ ስታዲየም ከሚገነባበት ቦታ በቅርብ ርቀት ነበር፡፡ ከውድድሩ መጠናቀቅ በኃላ ሁሉም ተሳታፊዎች ሜዳሊያ የወሰዱ ሲሆን ቀድመው ላጠናቀቁ የተወሰኑ ደጋፊዎች የክለቡ ዋነኛ አጋር የሆነው የሐበሻ ቢራን አርማ የያዘ የክለቡን ቡኒማና ቢጫ ቀለም ያለው ሰንደቅ አላማ ተበርክቶላቸዋል፡፡
ከውድድሩ መጠናቀቅ በኃላ የክለቡ የስታዲየም ግንባታ በሚያርፍበት ቦታ ላይ በተካሄደው የመሠረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ፕሮግራም ላይ የመክፈቻ ንግግርን ያደረጉት የክለቡ የቦርድ ፕሬዚዳንት የሆኑት መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ እንደተናገሩት ከሆነ የመሩጫው ቲሸርት ብዛት 10ሺህ ብለን መገመታችን ከሰፊው የደጋፊ ፍላጎት አንጻር እጥረት እንደፈጠረ ይህም ስህተት እንደነበረ አምነው በቀጣይ መሰለ ስህተቶች እንደማይደገሙና በጥቂት አመታት ውስጥ የዚህን አመታዊ ሩጫ ተሳታፊ ቁጥር እስከ መቶ ሺህ ለማድረስ እንደሚሠሩ ተናግረዋል ፤ አያይዘውም ይህ ከ35እስከ 40 ሺህ ተመልካች ማስተናገድ ይችላል የተባለለት ስታዲየም ግንባታው በ5 አመታት ጊዜ ውስጥ ተገንብቶ እንደሚያልቅም ገልፀዋል፡፡፡፡
በመቀጠል በ2009 የውድድር ዘመን ከዚህ አለም በሞት የተለዩትን ሶስቱን የኢትዮጵያ ቡና የልብ ደጋፊዎች እንዲሁም አሰግድ ተስፋዬን በማሰብ የህሊና ፀሎት ከተደረገ በኃላ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሳኒ ረዲ በንግግራቸው በኢትዮጵያ ክለቦች ደረጃ ፈርቀዳጅ የሆነውን የዚህን ስታዲየም መሠረተ ድንጋይ በማስቀመጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው ፤ እርሳቸው የሚመሩት ቡናና ሻይ ልማትና ግብይት ባለስልጣንም ዳግም ለክለቡ ጎን ቃላቸውን እንደሚያድሱ ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም አጠቃላዩ የቡና ሴክተር በሙሉ ከክለቡ ጎን መሆኑን አረጋግጠው ፤ ስታዲየሙ በተቀመጠለት ጊዜ እውን እንደሚሆን እርግጠኛ ነኝ ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ጁነይዲ ባሻ ይህ ደጋፊ አይደለም ስታዲየም ሌላ ነገር መገንባት የሚያስችል አቅም ባለቤት የሆነ ክለብ መሆኑን ተናግረው ፤ ክለቡ ከሀገርም አልፎ በአፍሪካ ደረጃ ሀገርን ማስጠራት የሚችል ክለብ መሆኑን ተናግረው ስታዲየሙ ሲጀመር ለማየት እንደበቁት ተጠናቆ ለምርቃቱ ያብቃን በማለት ተናግረዋል፡፡
በመቀጠል የእለቱ የክብር እንግዳ የነበሩት አቶ ሳሊም ረዲና ሌሎች የክብር እንግዶች በጋራ በመሆን የስታዲየሙን የመሠረተ ድንጋይ አስቀምጠዋል ፤ በስተመጨረሻም በስፍራው የተገኙት ደጋፊዎች እና የክለቡ አመራሮች በጋራ በመሆን የክለቡን መዝሙር በጋራ ዘምረው ፕሮግራሙ ፍጻሜውን አግኝቷል፡፡