የ2009 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ፍፃሜውን ዛሬ ሐምሌ 12 በድሬዳዋ ከተማ ያገኛል፡፡ የየምድቦቹ አላፊዎችም ለዋንጫው ይፋለማሉ፡፡
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በምድብ ሀ የውድድር አመቱን በሙሉ ከአናት ተቀምጦ በመቆየት በ64 ነጥቦች ፕሪምየር ሊጉን ሲቀላቀል ጅማ ከተማ በተመሳሳይ በምድብ ለ አመዛኙን የውድድር ዘመን በመሪነት ዘልቆ በ56 ነጥቦች ወደ ፕሪምየር ሊጉ መቀላቀል ችሏል፡፡
ወልዋሎ አርብ ረፋድ ላይ ወደ ድሬዳዋ ከተማ የገባ በመግባት ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን አስልጣኝ ብርሃኔ ገብርእግዛብሔርም በድሬዳዋ መልካም ትዝታዎች እንዳሏቸው ገልጸዋል፡፡ ” ከተለያዩ ቡድኖች ጋር ወደዚህች ከተማ መጥቻለው ከመድን ፣ አዳማ ፣ ኪራይ ቤቶች እና መቀለ ጋር … ከሁሉም ጋር ማለት ይቻላል ስኬትን አስመዝግቢያለው ፤ ከመቀሌ ጋር ግን ሳይሳካልኝ ቀርቶ ነበር፡፡ ከሞላ ጎደል በድሬዳዋ ላይ ስኬታማ ነበርኩኝ፡፡ ” ያሉት አሰልጣኙ ስለ ቡድናቸው ዝግጅትም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ” ለ5 ቀን ቅድመ ዝግጅት አድርገናል፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ጨዋታ 31ኛ ጨዋታችን ነው፡፡ ለዚህ ጨዋታ ብለን በተለየ መንገድ አልተዛጋጀንም ፤ እንደሁሉ ጊዜ እንደምነዘጋጀው ነው ያደረግነው፡፡ ነገር ግን የቡድኑ የመሻነፍ መነሳሳት ከፍተኛ ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ሁሉም የቡድኑ አባላት አየር ንብረቱን ተላምደዋል፡፡ ስለዚህ ጥሩና የተሻለ እንቅስቃሴ አድረገን እናሸንፋለን፡፡ በቡድኔ በኩል የተጎዳም ሆነ በቅጣት ዙሪያ ምንም ነገር የለንም” ብለዋል፡፡
ጅማ ከተማ እንደወልዋሎ ሁሉ ዓርብ አመሻሸ ላይ ወደ ድሬዳዋ ከተማ በመግባት ዝግጅት ሲያደርግ የቆየ ሲሆን የገባ ሲሆን አስልጣኝ መኮንን ገብረዮሐንስ ስለ ዛሬው ጨዋታ አጠቃላይ ዝግጅት እንዲህ ይላሉ፡፡
ቡድኔ በደንብ ዝግጀት እያደረገ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ይህ ጨዋታ የመጨረሻችን ነው፡፡ ዋንጫውን ለማንሳት የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን፡፡ ድሬዳዋ ሞቀታማ ሀገር ነች፡፡ ነገር ግን ጨዋታው ከቀኑ 10፡00 ላይ ስለሚደረግ የአየርንብረቱ ይከብደናል ብዬ አላስብም፡፡ ስለ ተጋጣሚ ቡድናችን የምለው ነገር ምንም ነገር የለም፡፡ ሁለታችንም የተለያየ ምድብ ላይ ነበርን፡፡ ስለዚህ ሳይንሱ በሚፈቅደው መንገድ ተጋጣሚያችንን ማጥናት ቀላል ነው፡፡ ”
“ከቡድኔ አባላት መካከል ሁለት ተጫዋች አጥተናል፡፡ አንዱን በጉዳት ሲሆን ሌላኛውን ደሞ በቅጣት ምክንያት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የአሰላለፍ ለውጥ ይኖራል ማለት ነው፡፡”
ጨዋታው ዛሬ 10፡00 በድሬዳዋ ስታድየም የሚካሄድ ሲሆን ከፍተኛ ሊጉም 482 ጨዋታዎች ካካሄደ ፣ 8 ወራት ከፈጀ ፣ 3 ክለቦችን ወደ ፕሪምየር ሊግ ካሳደገ ፣ 6 ክለቦችን ወደ አንደኛ ሊግ ከሸኘ በኋላ ፍጻሜውን የሚያገኝ ይሆናል፡፡