የኢትዮጵያ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ሐምሌ 5 ከተከፈተ ወዲህ ወልድያ በገበያው ላይ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡ 4 ተጫዋቾችንም በእጁ ማስገባቱን አረጋግጧል፡፡
በቅዱስ ጊዮርጊስ 6 የውድድር ዘመናት ያሳለፈው ተስፋዬ አለባቸው ከክለቡ ጋር የነበረውን ኮንትራት ማጠናቀቁን ተከትሎ ማረፊያውን ወልድያ አድርጓል፡፡ ተስፋዬ ለተከላካይ ክፍሉ ሽፋን በመስጠት አምና ጥንካሬውን ያሳየው የቡድኑ የመከላከል አጨዋወት ይበልጥ ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከተስፋዬ ጋር በቅዱስ ጊዮርጊስ አብሮ የተጫወተው ቢያድግልኝ ኤልያስ ከጅማ አባ ቡና ጋር ያለውን የአንድ አመት ውል አጠናቆ ወደ ሰማያዊ ለባሾቹ ያቀና ተጫዋች ነው፡፡ መልካም የውድድር አመት ያሳለፈው ቢያድግልኝ በበርካታ ጨዋታዎች ሳይቀያየር የዘለቀው የወልድያ የተከላካይ ክፍል ላይ ሰብሮ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ድሬዳዋ ከተማን ለመቀላቀል ተስማምቶ የነበረው ብሩክ ቃልቦሬ በአስገራሚ ሁኔታ ወደ ወልድያ አምርል፡፡ ለወልድያ መፈረሙን ተከትሎም ድሬዳዋ ከተማ ለፌዴሬሽኑ ቅሬታውን ማቅረቡ ታውቋል፡፡
ሰለሞን ገብረመድህን ሌላው ክለቡን የተቀላቀለ ተጫዋች ነው፡፡ የውድድር ዘመኑን ከጉዳት ጋር እየታገለ በፋሲል ከተማ ያሳለፈው ሰለሞን የወልድያ ችግር የሆነው የማጥቃት አጨዋወት ያሻሽለዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ወልድያ በውድድር አመቱ የደረጃ ሰንጠረዡን ይዞ እንዲያጠናቅቅ ከፍተኛውን ሚና የተጫወቱት ተከላካዩ አዳሙ መሐመድ እና ግብ ጠባቂው ኤምክሪል ቤሊንጌ ውላቸውን አድሰዋል፡፡
አመዛኞቹ ተጫዋቾች በ2009 መጀመርያ የተቀላቀሉ በመሆናቸው አንድ አመት ተጨማሪ ውል የሚቀራቸው መሆኑ አዲስ ከፈረሙት ተጫዋቾች ጋር ተደማምሮ በተጠናቀቀው የውድድር አመት ከሊጉ ክለቦች መካከል ጥቂት ተጫዋቾችን በመጠቀም ቀዳሚ የሆነው ወልድያ በ2010 የተሻለ የስብሰብ ጥልቀት ይዞ የሚቀርብ ይሆናል፡፡