በፕሪምየር ሊጉ 6ኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ፋሲል ከተማ ራምኬል ሎክ ፣ ፍሬው ጌታሁን ፣ ፊሊፕ ዳውዚ እና አቤል ውዱን አስፈርሟል፡፡
ራምኬል ሎክ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ለቆ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከተቀላቀለ በኋላ በመጀመርያው አመት በርካታ ጨዋታዎች ላይ የመሰለፍ እድል ቢያገኝም በተጠናቀቀው የውድድር አመት የቋሚነት ቦታውን ተነጥቋል፡፡ የሁለት አመት ኮንትራቱ መጠናቀቁን ተከትሎም ወደ ፋሲል ከተማ አምርቷል፡፡
ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ሌላው ለክለቡ የፈረመ ተጫዋች ነው፡፡ በ2007 የብሄራዊ ሊግ የማጠቃለያ ውድድር በአርሲ ነገሌ መለያ ባሳየው መልካም እንቅስቃሴ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተዛወረው ፍሬው በተለይ ዘንድሮ ሮበርት ኦዶንካራ በጉዳት ከሜዳ በራቀባቸው ጊዜያት የመሰለፍ እድል አግኝቶ ነበር፡፡ የፍሬው መፈረም በጉዳት እና የአቋም መዋዠቅ ምክንያት ሲቸገር የታየው የፋሲል የግብ ጠባቂ አማራጭ ያሰፋዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ወደ ፋሲል ያቀናው ሌላው ተጫዋች ያለፉትን አመታት በአማራ ውሀ ስራ ያሳለፈው አቤል ነው፡፡ የመሀል ተከላካዩ አቤል ከቀድሞ አጣማሪው ያሬድ ጋር በአጼዎቹ ቤት ዳግም የሚገናኝ ይሆናል፡፡
ናይጄርያዊው አጥቂ ፊሊፕ ዳውዚ ለክለቡ የፈረመ 4ኛው ተጫዋች ነው፡፡ በ2003 ኢትዮ ኤሌክትሪክን በመቀላቀል ወደ ኢትዮጵያ የመጣው ፊሊፕ በደደቢት እና ንግድ ባንክ አሳልፎ ወደ ኩዌት ካመራ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ለፋሲል ከተማ ፊርማውን አኑሯል፡፡