የ2009 የኢትዮዽያ ከፍተኛ ሊግ በጅማ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቀቀ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የመዝጊያ ጨዋታ ዛሬ በድሬዳዋ ስታድየም ተካሂዶ ጅማ ከተማ የአጠቃላይ አሸናፊ በመሆን አጠናቋል፡፡ የሀገሪቱን ትልልቅ ውድድሮች በተሳካ ሁኔታ በማዘጋጀት ከቅርብ አመታት ወዲህ ውጤታማ የሆነችው ድሬዳዋ ከተማም ይህን የከፍተኛ ሊግ ውድድርንም በማዘጋጀት በብቃት ተወጥታለች ።

በከፍተኛ ሊጉ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ከየምድባቸው አንደኛ በመሆን ያጠናቀቁት ጅማ ከተማ እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ባገናኘው የፍፃሜ ጨዋታ ጅማ ከተማ በአቅሌሲያስ ግርማ ብቸኛ ጎል 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡

የድሬዳዋ ከተማ ከንቲባ ፣ የጅማ ከተማ ከንቲባ ሱልጣን ዛኪር ፣ የድሬደዋ ወጣቶች ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ከድር ጁሀር ፣ የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት አቶ አበበ ገላጋይ እና አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በማርሽ ባንድ በታጀበው ደማቅ ስነ ስርአት በኢትዮጵያ ብሄራዊ መዝሙር በመዘመር ጨዋታው ተጀምሯል፡፡

በመጀመርያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ ወደ ጎል በመድረስ የተሻሉት ጅማዎች በኄኖክ መሃሪ እና በአቅሌሲያስ ግርማ አማካኝነት ጠንካራ የጎል ሙከራ ማድረግ የቻሉ ሲሆን ጫናቸው ፍሬ አፍርቶ በ22ኛው ደቂቃ ላይ አቅሌሲያስ ግርማ ላይ ፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍ/ቅ/ምት ራሱ አቅሌሲያስ ወደ ጎልነት በመቀየር ጅማ ከተማን ቀዳሚ ማድረግ ቻለ።


ከጎሉ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ወልዋሎዎች ተጭነው ቢጫወቱም ጠንካራውን የጅማ ተከላካይ ማለፍ ተስኗቸው ታይተዋል። ጨዋታውም በተደጋጋሚ በሚሰራ ጥፋት ምክንያት እየተቆራረጠ ዘልቆ ድጋሚ ጎል ሳይስተናገድበ በጅማ ከተማ 1-0 መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

ከእረፍት መልስ ወልዋሎዎች በሙሉ ኃይላቸው ለማጥቃት እና ጎል ለማስቆጠር ቢንቀሳቀሱም የማጥቃት መንገዳቸው ያልተደራጀ በመሆኑ የጅማን ተከላካዮች ሰብረው መግባት ተስኗቸው ታይቷል፡፡ አልፎ አልፎ የሚያገኙትን አጋጣሚም የጅማው ግብ ጠባቂ ቢንያም ታከለ አምክኗቸዋል፡፡ በአንፃሩ ጅማዎች በብቸኛ አጥቂነት በተሰለፈው አቅሌሲያስ ግርማ አማካኝነት ግብ ሊሆኑ የሚችሉ አጋጣሚዎችን ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይስተናገድበት ከእረፍት በፊት በተቆጠረ የአቅሌሲያ ግርማ ብቸኛ ጎል ጅማ ከተማ የ2009 የኢትዮዽያ ከፍተኛ ሊግ አጠቃላይ አሸናፊ በመሆን ጨዋታው ተጠናቋል።

የጨዋታውን ፍጻሜ ተከትሎ የሽልማት ስነስርአት የተካሄደ ሲሆን ለጅማ ከተማ የወርቅ ሜዳልያ እና የምድብ ለ አንደኛ በመሆኑ ዋንጫ ሲያገኝ በአጠቃላይ አሸናፊነቱ ደግሞ የከፍተኛ ሊግ አሸናፊ ዋንጫ ተቀብሏል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የብር ሜዳልያ እና የምድብ ሀ አንደኛ በመሆኑ የዋንጫ ተሸላሚ መሆን ሲችል መቐለ ከተማ በውድድሩ ሦስተኛ ሆኖ በመጨረሱ የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚ ሆናል።

የከፍተኛ ሊጉን ጨምሮ የኢትዮዽያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የኮከብ ተጫዋች እና ኮከብ ጎል አስቆጣሪ እንዲሁም የኮከብ አሰልጣኝ እና የስፖርታዊ ጨዋነት ተሸላሚዎች የገንዘብ እና የዋንጫ ሽልማት ወደ ፊት በሚገለፅ ቦታ እና ቀን በደመቀ ስነ ስርአት እንደሚፈፀም ይታወቃል ።

በመጨረሻም
ለሁለት ቀን ያህል በድሬደዋ ከተማ አስተናጋጅነት የአራቱም ክለቦች ደጋፊዎች በርከት ብለው በመምጣት የስፖርታዊ ጨዋነት መርህ ሳይጓደል በሰላም ተጀምሮ የተጠናቀቀ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም የከተማው አስተዳደር በማጠቃለያው ጨዋታዎች ላይ ለተሳተፉት ክለቦች የእራት ግብዣ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *