የኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ሰሞኑን መነጋገርያ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሰው የኤፍሬም ዘካርያስ ጉዳይ በቅርቡ እልባት እንደሚያገኝ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 30ኛ ሳምንት በመውረድ ስጋት ውስጥ ይገኝ የነበረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ወደ ሀዋሳ ተጉዞ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ ከጨዋታው አስቀድሞ በክለቡ ቅጣት ተጥሎበት ከሜዳ ርቆ የሚገኘው ኤፍሬም ዘካርያስ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ተጫዋቾች ጋር ውጤትን አላግባብ ለማግኘት ሲደራደር አግኝተነው ለህግ አቅርበነዋል ፤ ቅጣትም አስተላልፈንበታል ሲል የሀዋሳ ከተማ እግርኳስ ክለብ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎም ኤሌክትሪክ በሊጉ ሲቆይ ጅማ አባ ቡና እና ንግድ ባንክ ወደ ከፍተኛ ሊግ ሲወርዱ ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው ጅማ አባ ቡናም ፌዴሬሽኑ ጉዳዩን በጥልቀት መርምሮ ውሳኔ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡ ተጫዋቹ እና ኢትዮ ኤሌክትሪክ ደግሞ በጉዳዩ ላይ እንዳልተሳተፉ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጉዳዩን ለማጣራት 5 ግለሰቦችን የያዘ ኮሚቴ አዋቅሮ ላለፉት 10 ቀናት የራሱን ምርመራ ሲያደርግ የቆየ ሲሆን ስፍራው ድረስ በመጓዝም ከሀዋሳ ከተማ ፣ የጉዳዩ ዋንኛ ተሳታፊ ነው ከተባለው ኤፍሬም ዘካርያስ እንዲሁም በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩል ድርድሩ ላይ ተሳትፈዋል ከተባሉ ተጫዋቾች እና ሌሎች ከጉዳዩ ጋር ተያያዥ ከሆኑ አካላት ጋር ቀርቦ በመነጋገር እና ማስረጃዎች በመሰብሰብ ጉዳዩን ሲመረምር እንደቆየ ተገልጿል፡፡
የኮሚቴው የምርመራ ስራ ወደ መጠናቀቂያው እንደደረሰ ሲገለጽ ውጤቱንም በቅርብ ቀናት ውሰጥ በጋዜጣዊ መግለጫ ለስፖርት ቤተሰቡ እንደሚያሳውቅ ተነግሯል፡፡