የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 24ኛ ሳምንት ቀሪ 5 ጨዋታዎችን ዛሬ አስተናግዶ የሐረር ሲቲን ወራጅነት አውጇል፡፡
በአዲስ አበባ ስታዲየም ነ9፡00 መብራት ኃይልን የገጠመው ኢትዮጵያ መድን ከረጅም ጊዜያት በኃላ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል፡፡ አሰልጣኝ አስራት ኃይሌን ማሰናበቱ የተነገረው መድን በጊዜያዊው አሰልጣኝ እየተመራ ከመልካም እንቅስቃሴ ጋር 2-1 አሸንፎ ወጥቷል፡፡ ግብ በማስቆጠር ቅድሚያውን የያዙት መብራት ኃይሎች ሲሆኑ በ8ኛው ደቂቃ ናይጄርያዊው አዎይኒ ሚካኤል የቀዮቹን ግብ አስቆጥሯል፡፡ ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በሰራው አደገኛ ፋውል በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል፡፡ ለሰማያወዎቹ የድል ግቦቹን አምበሉ ወንድይፍራው ጌታሁን ከእረፍት በፊት ፣ በአስራት ኃይሌ ተጠባባቂ ወንበር አሟቂ ሆኖ የከረመው አስራት ሸገሬ በሁለተኛው አጋማሽ አስቆጥረዋል፡፡
ቀጥሎ በተደረገው ጨዋታ ወላይታ ድቻን ያስተናገደው መከላከያ በተጨማሪ ሰአት በተቆጠረ ግብ አቻ ወጥቷል፡፡ በወላይታ ድቻ ደጋፊዎች ህብረ ዝማሬ እና አዲስ ማልያ በደመቀው ጨዋታ ከእረፍት መልስ ወላይታ ድቻዎች በባዬ ገዛኸኝ በ5 ደቂቃዎች(58ኛ እና 63ኛ ደቂቃ) ውስጥ በተቆጠሩ ሁለት ግቦች (የሁለተኛዋ ግብ በመከላከያው ተከላካይ አወል አብደላ ተጨርፋለች) መምራት ቢችሉም ተቀይሮ የገባው በዳሶ ሆራ በ76ኛው ደቂቃ ከመረብ ያሳረፋት ግብ መከላከያዎችን ወደ ጨዋታው መልሳቸዋለች፡፡ ድቻዎች በጥልቀት ወደ ኋላ አፈግፍገው በመከላከል ውጤታቸውን አስጠብቀው ለመውጣ ትግል ቢያደርጉም በተጨማሪ ደቂቃ ሙሉአለም ጥላሁን በግንባሩ ገጭቶ ያስቆጠራት ግብ ሊያሸንፉ የተቃረቡትን ጨዋታ በአቻ ውጤት እንዲያጠናቅቁ አስገድዷቸዋል፡፡
ሐረር ላይ አርባምንጭ ከነማን ያስተናገደው ሐረር ሲቲ 2-0 ተሸንፎ ከፕሪሚየር ሊግ መውረዱን አረጋግጧል፡፡ ለአርባምንጭ ከነማ ግቦቹን ያስቆጠሩት ሙሉአለም ጥላሁን እና ተመስገን ዱባ ናቸው፡፡ ከ1995 የውድድር ዘመን ጀምሮ ላለፉት 12 ተከታታይ የውድድር ዘመናት በፕሪሚየር ሊጉ የቆየው ሐረር ሲቲን ለከርሞው የምናየው በከፍተኛው ብሄራዊ ሊግ ነው፡፡
ፋሲለደስ ላይ ዳሽን ቢራ በውጤት ማጣት ጉዞው ቀጥሏል፡፡ ዘንድሮ በሜዳው 2 ጨዋታ ብቻ ያሸነፈው ዳሽን ቢራ ኢትዮጰያ ቡናን አስተናግዶ 1-0 ተሸንፏል፡፡ ለኢትዮጵያ ቡና ብቸኛዋን ግብ አስቻለው ግርማ ከመረብ አሳርፏል፡፡
አሰላ ላይ ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው ሙገር ሲሚንቶ 2-2 አቻ በመለያየት ደረጃውን በአንድ ከፍ አድርጓል፡፡
ሊጠናቀቅ የሁለት ሳምንት እና የ2 ተስተካካይ ጨዋታዎች እድሜ ብቻ የቀረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግን ከላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ65 ከታች ደግሞ መድን በ13 ይመራሉ፡፡