​’ ለሴቶች ትኩረት እንስጥ ‘ የፉትሳል ውድድር ዛሬ ተጠናቀቀ

‘ ለሴቶች ትኩረት እንስጥ ‘ በሚል መሪ ቃል በአሰልጣኝ ዘላለም ፀጋዬ አዘጋጅነት ሲከናወን የነበረው የሴቶች የፉትሳል ውድድር ዛሬ ፍፃሜውን አግኝቷል።

ለሁለተኛ ጊዜ በሰባት ክለቦች መካካል በተከናወነው ይህ ውድድር በዋናው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚሳተፉ የክለብ ተጨዋቾችን ፣ አሰልጣኞችን እንዲሁም ታዋቂ የቀድሞ ተጨዋቾችን በማካተት ነበር ሲከናወን የቆየው፡፡

በባምቢስ ሜዳ ዛሬ የደረጃ እና የፍፃሜ ጨዋታዎቹ ሲካሄዱ በዝናብ ምክንያት ሜዳው  ለጨዋታ ምቹ ባለመሆኑ ይጀመራሉ ተብሎ ቅድሚያ መርሃ ግብር ከወጣለት ሰዓት ዘግይተው ነበር ጨዋታዎቹ የተደረጉት።

በደረጃ ጨዋታው ፍሬንድስ ኤልሳ እና ጓደኞቿን 7-2 በማሸነፍ ሶስተኛ ደረጃ ይዞ ማጠናቀቁን ሲያረጋግጥ ጥሩ የጨዋታ እንቅቃቅቃሴ በተስተዋለበት እና የደጋፊዎች ቀልብ በገዛው የፍፃሜ ጨዋታ እሙዲ እና ጓደኞቿ ፍሬን 14-9 በሆነ ውጤት በማሸነፍ የዋንጫው ባለቤት ሆነዋል፡፡ በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ብርቱ ፉክክር ሲያደርጉ መደበኛ የጨዋታው ክፍለ ጊዜ 8-8 በሆነ አቻ ውጤት በመጠናቀቁ ወደ ጭማሪ ሰዓት በማምራት ነበር አሸናፊ ቡድኑ የተለየው፡፡

በርካታ የስፖርት ቤተሰብ በባምቢስ ሜዳ በመገኘት ውድድሩን ያደመቀ ሲሆን ከጨዋታዎቹ በኃላ ስዩም ከበደ፣ እየሩሳሌም ነጋሽ እና ሌሎች የክብር እንግዶች በተገኙበት የሽልማት ስነስርዓቱ ተከናውኗል፡፡ ሶስተኛ ለወጣው ፍሬንድስ ቡድን የ1000 ሺ ብር እንዲሁም ሁለተኛ ለወጣው ፍሬ የ2000 ሺ ብር ሽልማት ሲሰጣቸው ውድድሩን በበላይነት አንደኛ ሆኖ ላጠናቀቀው እሙዲ እና ጓደኞቿ ቡድን የዋንጫ እና የ8000 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በውድድሩ 22 ጎሎችን በማስቆጠር የቀዱስ ጊዮርጊስ አጥቂ የሆነችው ሜሮን አብዶ (ከእሙዲ እና ጓደኞቿ ቡድን) ኮከብ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የዋንጫ ተሸላሚ ስትሆን የቀድሞዋ የብሄራዊ ቡድን ኮከብ ሰሚራ ከማል የውድድሩ ኮከብ ተጨዋች በመባል በተመሳሳይ የዋንጫ ተሸላሚ ሆናለች፡፡ በውድድሩ ድንቅ አቋማን ስታሳይ የነበረችው የፍሬ ቡድን ተጨዋች ሶፋኒት ተፈራ ወጣት ኮከብ ተጫዋች በመባል የማልያ ሽልማት ተበርክቶላታል፡፡


ውድድሩ ቀጣይነት እንዲኖረው በአመት ሁለት ጊዜ የማድረግ ሃሳብ እንዳላቸው የተናገሩት የውድድሩ አዘጋጅ አሰልጣኝ ዘላለም ፀጋዬ ከባለፈው አመት በተሻለ ዘንድሮ የተሳታፊ ቡድኖችም ቁጥር ከ4 ወደ 7 ማደጉ ደስ እንዳሰኛቸው ነገር ግን ይህ በቂ እንዳልሆነ እና በቀጣይ የተሳታፊ ቡድኖች ቁጥር ለማሳደግ ስራዎችን እንደሚሰሩ ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *