​ጸጋዬ ኪዳነማርያም የአርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ሁለተኛ ዙር ደካማ አቋም ያሳየው አርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ ጸጋዬ ኪዳነማርያምን ቀጣዩ የክለቡ አስልጣኝ አድርጎ ቀጥሯል፡፡

ክለቡ የውድድር ዘመኑን በአሰልጣኝ ጳውሎስ ጸጋዬ መሪነት ጀምሮ ቀስ በቀስ የውጤት ቀውስ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ አሰልጣኙን በማሰናበት በምክትሉ በረከት ደሙ መሪነት እንዲቀጥል ተደርጎ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ በውድድር አመቱ አጋማሽ ከንግድ ባንክ ጋር የተለያዩት ጸጋዬ ኪዳነማርያምን ለመቅጠር ድርድር ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ ሀዋሳ ላይ በተደረገ ስምምነት ቀጣዩ የአርባምንጭ ከተማ አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል፡፡ በረከት ደሙ ደግሞ የአሰልጣኝ ጸጋዬ ረዳት ሆኖ የሚቀጥል ይሆናል፡፡

ጸጋዬ ኪዳነማርያም በትራንስ ኢትዮጵያ የአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ረዳት ኋላ ላይ ደግሞ ዋና አሰልጣኝ ሆነው በመስራት የፕሪምየር ሊግ አሰልጣኘነት ህይወትን የጀመሩ ሲሆን በሐረር ቢራ 7 የውድድር ዘመናት ካሳለፉ በኋላ በ2005 ለአጭር ጊዜ ኢትዮጵያ ቡናን አሰልጥነዋል፡፡ ቀጥሎም እስከተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቆይታ አድርገዋል፡፡

አርባምንጭ ከተማ እንደሌሎች አመታት ሁሉ በዝውውር መስኮቱ ላይ እየተሳተፈ የማይገኝ ሲሆን እስካሁን ምንም ተጫዋች ማስፈረም አልቻለም፡፡ ሆኖም አሰልጣኝ ጸጋዬ ከመጪው ሳምንት ጀምሮ ለክለቡ የሚያስፈልጉ ተጫዋቾችን የመመልመል ስራ እንደሚጀምሩ ታውቋል፡፡

2 Comments

 1. ይህ መልክቴ ነው
  “” ኳስን በማንጠባጠብና አብዶ በመስራት የሚያኮሩ ታዳጊና በቂ ስፖርተኛ ባለበት ከተማ የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው ተረት አታስተርቱብን የአከባቢውን ስፖርተኞች አትግደሉቡን “”

  1. ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ለእግር ኳስ ልዩ ውበት ፈጣሪ የሆኑትን የአከባቢውን ልጆች በመተው ከውጭ ተጫዋች ማስፈረሙ ተተኪ ስፖርተኞችን 100% ያሳጣናል
   ክለቡ ተተኪ ታዳጊዎችን ይመልከት ለአዲሱ አሰልጣኝ
   በብሔራዊ ቡድናችንና በተለያዩ ክለቦች የአርባ ምንጭ ልጆች ቀዳሚውን ድርሻ እንደሚይዙ እንደስማቸው አንበሶች ናቸው::
   ለእግር ኳስ ልዩ ውበት ፈጣሪ ናቸው
   በሀገራችን በእግር ኳስ ስፖርት የማይረሱ ስፖርተኞችን አርባ ምንጭ ማበርክቷን
   ስንታየሁ ቆጬ : መሳይ ታፈሪ የአሁኑ የወላይታ ዲቻ አሰልጣኝ….. ለብሔራዊ ቡድናችን ዋልታና ቋሚ በመሆን የግንብ አጥር የሚሰሩት አበባው ቡጣቆ ፣ ለረጅም አመታት በጥሩ አቋም የዋልያዎቹ አንበል 2013 የአለም ታዋቂውን ሽልማት ፊፋ ባሎን ዶር እጩ ደጉ ደበበ ፣ ገረሱ ሻሜና አፈወርቅ ተስፋየ ፈጠነ ቢያድግልኝ ተሾመ እንዲሁም በተተኪው በብሔራዊ ቡድናችን ጉልህ ድርሻ ያላቸው አንበሉ ሙሉአለም መስፍን እና ገ/ሚካኤል ያቆብ የመሳሰሉት የአርባ ምንጭ ትሩፋቶች እንደሆኑና
   ከነዚህ በላይ ኳስን በማንጠባጠብና አብዶ በመስራት የሚያኮሩ ታዳጊና በቂ ስፖርተኛ ባለበት ከተማ የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው ተረት አታስተርቱብን የአከባቢውን ስፖርተኞች አትግደሉቡን

Leave a Reply