በ2018 በፈረንሳይ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአለም ከ20 አመት በታች ዋንጫ ለመካፈል በመጀመርያ ዙር ማጣርያ የኬንያ እና ቦትስዋናን አሸናፊ የምትገጥመው ኢትዮጵያ እስካሁን በብሐራዊ ቡድኗ ላይ ያለውን ሁኔታ ሳታሳውቅ ቆይታለች፡፡
ሶከር ኢትዮጵያ ከፌዴሬሽኑ ባገኘቸው መረጃ በሐምሌ ወር የመጨረሻ ቀናት የአሰልጣኝ ቅጥር እንደሚካሄድ የታወቀ ሲሆን በክፍት ስራ ማስታወቂያ ይሁን አልያም በጥቆማ ለመምረጥ እንዳልተወሰነ ግን ተነግሯል፡፡ ሒደቱ ቶሎ ከተጠናቀቀም ከማጣርያው ጨዋታ አንድ ወር ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ተቀጥሮለት ወደ ዝግጅት ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ በመጀመርያው ዙር ማጣርያ ከኬንያ እና ቦትስዋና አሸናፊ መስከረም 5 ቀን 2010 በሜዳዋ የምታደርግ ሲሆን የመልሱን ጨዋታ ከ15 ቀናት በኋላ ከሜዳዋ ውጪ የምታደርግ ይሆናል፡፡ በቅድመ ማጣያው ኬንያ ወደ ቦትስዋና አምርታ 7-1 ማሸነፏን ተከትሎም ቀጣይ የኢትዮጵያ ተጋጣሚ ለመሆን ከጫፍ ደርሳለች፡፡
በ2016 በፓፓዋ ኒው ጊኒ አስተናጋጅነት በተካሄደው የአለም ከ20 አመት በታች ሴቶች ዋንጫ ማጣርያ ኢትዮጵያ ካሜሩን እና ቡርኪናፋሶን በመርታት ወደ መጨረሻው ማጣርያ አልፋ በጋና 6-2 አጠቃላይ ውጤት ተሸንፋ ከአለም ዋንጫው ቀርታለች፡፡ በማጣርያው ኢትዮጵያ ያስቆጠረቻቸውን 6 ግቦች በሙሉ ሎዛ አበራ ማስቆጠሯም የሚታወስ ነው፡፡