​የእለቱ አጫጭር ዝውውር ዜናዎች – ሐምሌ 18 ቀን 2009 

ሲዳማ ቡና

– ሲዳማ ቡና የውድድር ዘመኑን በሀዋሳ ከተማ ያሳለፈው ወንድሜነህ አይናለምን አስፈርሟል፡፡ በ2008 በከፍተኛ ሊጉ ለደቡብ ፖሊስ ድንቅ አቋሙን አሳይቶ ወደ ሀዋሳ ተዛውሮ የነበረው ወንድሜነህ በክለቡ የመሰለፍ እድል ሳያገኝ ክለቡን ለቆ ለሲዳማ ፊርማውን አኑሯል፡፡

– ሶስት ጋናዊያን ተጫዋቾች ለማስፈረም ከስምምነት የደረሰው ሲዳማ ቡና ተጨማሪ ጋናዊ አጥቂ ለማስፈረም ተቃርቧል፡፡ ለኮንትራት ማደሻ ከፍተኛ ገንዘብ የጠየቀውና ክለቡን እንደሚለቅ የሚጠበቀው ላኪ ሰኒን የሚተካ አጥቂ ይሆናል ተብሎም ይጠበቃል፡፡

ኤሌክትሪክ

ከቀናት በፊት ለኤሌክትሪክ ለመጫወት የተስማማው ግርማ በቀለ በይፋ ፊርማውን ለክለቡ አኑሯል፡፡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከግርማ በተጨማሪ በተከላካይ ስፍራ ላይ ሞገስ ታደሰን ማስፈረሙ የሚታወስ ነው፡፡ 

አዳማ ከተማ

ክሪዚስቶም ንታምቢ እና አላዛር ፋሲካን ያስፈረመው አዳማ ከተማ ዳንኤል ተሾመን አስፈርሟል፡፡ አዳማ ከተማ የጃኮ ፔንዜ እና በሽር ደሊልን ኮንትራት ያራዘመ ሲሆን ወደ ድሬዳዋ ባመራው መክብብ ምትክ የቀድሞ የአአ ከተማ ግብ ጠባቂ ዳንኤልን ማስፈረም ችሏል፡፡

ድሬዳዋ ከተማ

– በትላንትናው እለት ጀማል ጣሰውን ያስፈረመው ድሬዳዋ ከተማ ተጨማሪ ግብ ጠባቂ አስፈርሟል፡፡ የውድድር ዘመኑን ከሀዋሳ ከተማ ወደ አዳማ ከተማ በውሰት ተዛውሮ ያሳለፈው መክብብ ደገፉ ክለቡን በለቀቀው ቢንያም ሐብታሙ ምትክ ክለቡን ተቀላቅሏል፡፡

– በወልድያ መልካም የውድድር አመት ያሳለፈው ያሬድ ዘውድነህ ከወልድያ ጋር መለያየቱ ተነግሯል፡፡ ወደ ትውልድ ከተማው አምርቶ ለድሬዳዋ ከተማ ሊፈርም እንደተቃረበም ተሰምቷል፡፡

ብሩክ ቃልቦሬ 

– ባለፈው ሳምንት ለወልዲያ ፊርማውን ያኖረው ብሩክ ቃልቦሬ ጉዳይ እየከረረ መጥቷል፡፡ ተጫዋቹ ለክለባችን ፈርሞ ወደ ወልዲያ በማምራቱ ህግ ጥሷል በሚል ድሬዳዋ ከተማ ክስ ማቅረቡ የሚታወስ ሲሆን ብሩክ በበኩሉ ከወልዲያ ጋር በቃል ከመስማማት ውጪ አልፈረምኩም ብሏል፡፡ ይህንን ተከትሎም ድሬዳዋ ከተማ የተጫዋቹን ፊርማ ለማረጋገጥ የፈረመበትን ወረቀት ለፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ መላኩ ታውቋል፡፡

ወልዲያ

– በዝውውር መስኮቱ ለደርዘን የቀረቡ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ወልዲያ ዳዊት ፍቃዱን ለማግኘት እየተንቀሳቀሰ ነው ተብሏል፡፡ ተጫዋቹ ከአልጣኝ ዘማርያም ጋር መታየቱም ወደ ክለቡ እንደሚያመራ ፍንጭ የሰጠ ሆኗል፡፡

ጅማ ከተማ

– ሁለት ተጫዋቾችን ያስፈረመው ጅማ ከተማ ከከፍተኛ ሊጉ ተጫዋቾችን ለማስፈረም እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ ዘንድሮ በሀዲያ ሆሳዕና ጥሩ ጊዜን ያሳለፈው እንዳለ ደባልቄን ያስፈረመ ሲሆን ሌሎች የሆሳዕና ተጫዋቾች የሆኑት አሚኑ ነስሩ እና ሳምሶን ቆልቻም ለጅማ ከተማ ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ ተነግሯል፡፡

አርባምንጭ ከተማ

ጸጋዬ ኪዳነ ማርያምን አሰልጣን አድርጎ የቀጠረው አርባምንጭ ከተማ ተጫዋቾችን ለማስፈረም እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ በአመቱ አጋማሽ ወደ ንግድ ባንክ ተመልሶ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ቢንያም አሰፋ ከክለቡ ጋር ስሙ ሲያያዝ የውጪ ዜጋ ተጫዋቾችንም ለማስመጣት እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *