ኢትዮጵያዊው አማካይ ቢኒያም በላይ በጀርመኑ የቡንደስሊጋ 2 ክለብ በሆነው ኤዘንበርገር አወ የነበረውን የሁለት ቀናት የሙከራ ግዜ አጠናቆ ወደ ኦስትሪያ ለሌላ ሙከራ ሰኞ እለት አምርቷል፡፡
ቢኒያም በኤዘንበርገር ቆይታው እምብዛም በጨዋታዎች የመታየት እድልን አለማግኘቱን ተከትሎ ክለቡ ውል ሳያቀርብለት ቀርቷል፡፡ ክለቡ አዲሱ የቡንደስሊጋ 2 የውድድር ዘመን በሚቀጥለው ሳምንት ከመጀመሩ በፊት የመጨረሻ አቋም መለኪያውን ያለፈው እሁድ ከአራተኛ ዲቪዚዮኑ ክለብ ቪኤፍቢ ኦርባ ጋር አድርጎ 1 አቻ ሲለያይ ቢኒያም በሁለተኛው አጋማሽ ተሰልፎ ለ45 ደቂቃዎች መጫወት ችሏል፡፡ በተሰጠው ግዜ ተሰፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ቢያሳይም ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ኤዘንበርገር ቢኒያምን የማስፈረሙ ፍላጎት የተቀዛቀዘ ሆኗል፡፡ ሆኖም የክለቡ ስራ አስፈፃሚ ሊዮንሃርድት እና ዋና አሰልጣኙ ቶማስ ሌትስች በቢኒያም ብቃት መደነቃቸው ተነግሯል፡፡
የኤዘንበርገር አወ የሙከራ ግዜው አለመሳካቱን ተከትሎ ቢኒያም ወደ ታላቁ የኦስትሪያ ክለብ ሬድ ቡል ሳልዝበርግ ለሙከራ አቅንቷል፡፡ የኦስትሪያ የሊግ ውድድር (ቲፒኮ ቡንደስሊጋ) ባሳለፍነው ሳምንት የተጀመረ ሲሆን ለቢኒያም የሙከራ እድል የሰጠው የሳልዝበርግ መጋቢ ክለብ የሆነው ኤፍሲ ላይፈሪንግ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በርካታ ታዳጊ ተጫዋቾችን ለኦስትሪያ ሊግ ቻምፒዮኑ ሳልዝበርግ የሚመግበው ላይፈሪንግ በኦስትሪያ ሁለተኛ ዲቪዚዮን (ስካይ ጎ ኢርስት ሊጋ) ይወዳደራል፡፡ ላይፈሪንግ በመጀመሪያ ሳምንት የሊግ ጨዋታው ካፕፌንበርገርን 2-1 ሲረታ የኦስትሪያ የሊግ እና የጥሎ ማለፉ ባለድል ሳልዝበርግ ዎልፍስበርገርን ከሜዳው ውጪ 2-0 አሸንፏል፡፡ ሳልዝበርግ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ወደ ምድብ ለመግባት በማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ ይገኛል፡፡