​አሁን የት ይገኛሉ? አህመድ ጁንዲ

አሁን የት ይገኛሉ? አምዳችን ከዛሬ ጀምሮ በየሳምንቱ ማክሰኞ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ አሻራቸውን ያስቀመጡ ግለሰቦችን በማንሳት የሚቀርብ ይሆናል፡፡ በአምዱ ላይም አሁን ስለሚገኙበት ሁኔታ በእግርኳስ ስላሳለፉት ህይወት እና ተያያዥ ጉዳዮች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ፡፡

በዛሬው መሰናዷችን በሊጋችን ከታዩ ምርጥ አጥቂዎች ጎራ የሚመደበው አህመድ ጁንዲን አቅርበንላችኋል፡፡ ግብ አነፍናፊው አህመድ በምድር ባቡር ስሙን መተከል የቻለ አጥቂ ሲሆን በክለቡ ቆይታውም በ1991 የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ፣  በ1988 እና 1995 ደግሞ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል፡፡

ለ15 አመታት በላይ በተጫዋችነት ከቆየ በኋላ በ2003 ከእግርኳስ አለም የተገለለው አህመድ ጁንዲ ስእግርኳስ ህይወቱ ፣ ስለ አጥቂነት ፣ ስለ ድሬዳዋ እና ኢትዮጵያ እግርኳስ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ከእግርኳስ ከተለየህ በኋላ ከእይታ ርቀሀል፡፡ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለህ?

በአሁን ሰአት የድሬዳዋ ከተማ ከ20 አመት በታች ቡድንን እያሰለጠንኩ እገኛለው። የአሰልጣኝነት ኮርስ ወስጃለው፡፡ የድሬደዋ እግርኳስን ለማሳደግ ከህዝቡ እና ከአመራሮቹ ጋር በመሆን ታዳጊዎች ላይ መስራት እፈልጋለው። አንዳንድ የሚጎሉኝ ነገሮች አሉ ፤ እሱን ድጋፍ የሚያደርጉልኝ ፈልጌ አቅሙም ሙያውም ስላለኝ ባለሁበት አካባቢ በእኔ ስም ታዳጊዎችን እያሳደግኩ ማውጣት እፈልጋለው፡፡

በተጫዋችነት ዘመንህ ብዙ ጎል ካስቆጠሩና በተከላካዮች ከሚፈሩ ተጨዋቾች አንዱ ነበርክ፡፡ አንተን ላልተመለከቱ ሰዎች እራስህን እንዴት ትገልፀዋለህ ?  ምን አይነት አጥቂስ ነበርክ ?

እኔን አይተው ለማያቁ ትውልዶች ስለ እኔ በወቅቱ ስለነበረኝ ታሪክ እንዲህ የሚባል ሰው ነበር የሚለውን ማሳወቂያ መንገድ ሚዲያው መሆን ነበረበት። በወቅቱ ምን እንደነበርኩ ምን እንደሰራው ለትውልዱ የሚያስተላልፈው ሚዲያ ነው ብዬ አስባለው። እኔን የሚያውቀኝ ያቀኛል ፤ ለማያውቀኝ ግን ራሴን ለመግለፅ ያህል እኔ በነበርኩበት ዘመን በእውነቱ መጫወት ከባድ ነበር ሁሉም ቡድኖች ውስጥ የነበረው ስብስብ ጠንካራ ነበር። እኔ በምጫወትበት ወቅት በጣም አስቸጋሪ ተጨዋች ነበርኩ ፣ ጎል ካላስቆጠርኩ የምናደድ ተጫዋች ነበርኩ፡፡ አባቴ ሳይቀር ጎል ካገባው የሚያመሰግነኝ ካላገባው ደግሞ ‘አለቀልኝ’ የምልለት አይነት ሰው ነበር፡፡ ጎል ለማስቆጠር ከፍተኛ ፍላጎቱ የነበረኝ ፣ ተከላካዮችን በጣም የማስጨንቅ በነበረኝ ጉልበት እና ጎል የማስቆጠር አቅም የተነሳ አሰልጣኞች ሳይቀር ‘እሱን ያዙት እሱ ከተያዘ ቡድኑ ይቆማል ይባል ነበር። እንዲያውም አንድ ወቅት ከንግድ ባንክ ጋር እየተጫወትን በመጨረሻው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥሬ ምድር ባቡር አሸነፈ። ጨዋታው ካለቀ በኋላ ግብ ጠባቂው መጥቶ ምን አለኝ መሰለህ? ባቡር ሳይሆን አንተ ነህ ያሸነፍከን ያለኝን ጊዜ  አስታውሳለው። በአጠቃላይ በየአመቱ አስራ አምስት ፣ ሀያ ከዛ በላይ ጎል እያስቆጠርኩ ለከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት እፎካከር የነበርኩ ተጨዋች ነኝ።

ምን አይነት ግብ አስቆጣሪ ነበርክ?

እኔ ጎል የማስቆጥረው ከተለያዩ አቅጣጫዎች ነው፡፡ በተለይ የእኔ ኳሶች ጠንካራ ጉልበት ያላቸው ስለነበሩ ግብ ጠባቂዎች ለመመለስ ይቸገሩ ነበር። ጎል ሳስቆጥር እንዲሁ በጭፍን አልነበረም የምመታው ፤ የኳሱን ብልት አይቼ ነው።  የግብ ጠባቂውን ሁኔታ ፣ ጎሉ የት ጋር ነው ብዬ አይቼ ተረጋግቼ ነው የምመታው። በወቅቱም በግሌ አሰልጣኝ ከሚሰጠን ስልጠና ውጭ ጎል እንዴት ማስቆጠር እንዳለብኝ በአንድ ጎል ላይ ሦስት ግብ ጠባቂዎችን አቁሜ እለማመድ ነበር፡፡ ያ ነው ጥሩ አጥቂ ያደረገኝ።

የእግር ኳስ ህይወትህ በአመዛኙ በምስራቅ ኢትዮዽያ ክለቦች በተለይ በምድር ባቡር በመጫወት ነው ያለፈው። አንተን ከድሬዳዋ እንደወጡት ሌሎች ተጫዋቾች በተለያዩ ክለቦች ያልተመለከትንበት ምክንያት ምንድነው ?

አዎ እውነት ነው፡፡ ለምድር ባቡር እየተጫወትኩ ብዙ ክለቦች አናግረውኝ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ፣ ባንክ ፣ ጊዮርጊስ እና ኒያላ ያናግሩኝ ነበር፡፡ ሆኖም በዛን ወቅት በምድር ባቡር ውስጥ ቋሚ ሰራተኛ ነበርኩ፡፡ የሚከፈለኝ ደግሞ በሰራተኝነቴ ለብቻ በተጫዋች በመሆኔ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ከፍተኛ ክፍያ ይከፈለኝ ስለነበር ነው፡፡ ከዚህ ውጭ (ከምድር ባቡር) ወጥቼ መጫወት አልፈለኩም ፤ በባቡር የተሻለ ስለሚከፈለኝ። ሌላው ሚስት አግብቼ ልጅ ወልጄ እኖር ነበርና ከእነሱ ላለመራቅ ለዛ ነው ወደ ሌሎች ክለብ ወጥቼ ያልተጫወትኩት። ያም ቢሆን ግን ምድር ባቡር 1995 ላይ ከሊጉ ወርዶ በዛው ሲፈርስ ወደ ሐረር ቢራ አመራሁ፡፡ ከዛም ሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ተጫውቼ በመቀጠልም ወደ የመን እና ጅቡቲ ሄጄ ስመለስ ከ2002-2003 ለድሬደዋ ከተማ ተጫውቼ ከኳስ አለም ተገልያለሁ ።

እንደ ምርጥ አጥቂነትህ በብሔራዊ ቡድን ብዙም አልታየህም፡፡ ከድሬዳዋ ወጥተው በአአ ክለቦች እንደተጫወቱት በርካታ ተጫዋቾች አንተም ወደ አአ ክለቦች አለመዛወርህ በብሔራዊ ቡድን ብዙ ጊዜ እንዳናይህ አድርጓል ብለህ ታስባለህ ?

በእውነቱ ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት የግድ አአ የሚገኝ ክለብ ተጨዋች መሆን የለብህም ነበር፡፡ በየክልል ክለቦች ለሚጫወቱ ተጨዋቾች ብዙም ትኩረት አይደረግም፡፡ መጥተው የማየትም ፍላጎት የላቸውም። በእውነት በጣም የሚገርምህ እና ከህይወቴ የማልረሳው አንድ ነገር ልንገርህ የኢትዮዽያ ከፍተኛ ጎል አግቢ ሆኜ በጨረሱኩበት አመት (1988) የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ከሞሮኮ ጋር ለመጫወት ወደ ጣልያን ሲሄድ ተመርጬ ቪዛ ተመቶልኝ አውሮፕላን ውስጥ ልገባ ስል በሚገርም ሁኔታ አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ቀነሰኝ፡፡ እንዴት ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ተጨዋች ትቀንሳለህ ሲባል ባዩ ሙሉን ከቤልጅየም መርጫለው አለ፡፡ በጣም ይገርማል። ሆኖም አልፎ አልፎ አጋጣሚውን አግኝቼ ስመረጥ ግብፅ ላይ ተጫውቻለው ከታንዛንያ እና ከሱዳን ጋር ተሰልፌ ተጫውቻለው፡፡ ግን በአብዛኛው አአ ስትጫወት ነው ትኩረት የሚደረገው አሁንም ይህ አሰራር አለ፡፡ ይህ መስተካከል አለበት የሚችል ተጫዋች ከየትኛውም ቦታ መመረጥ አለበት።

በእናንተ ወቅት ድሬዳዋ የበርካታ ባለክሎት ተጨዋቾች መፍለቂያ ነበረች። አሁን ላይ ድሬዳዋ ከተማ እንኳን በተጨዋቾች ግዢ ላይ የተጠመደ ቡድን ነው። ለድሬዳዋ ተስጥኦ መንጠፍ ምክንያቱ ምንድነው?  ይህን ስትመለከትስ ምን ይሰማሀል?

እንደ አማራጭ ነው የምትወስደው አንድ ነገር ስር መሰረቱን ታዳጊ ላይ ጥለኸው ካላመጣህ በስተቀር ትልቁን ፕሪምየር ሊግ ለመጫወት ከባድ ነው፡፡ በመጀመርያ መሰረት ያስፈልገል። አሁን ጥሩ የታዳጊ ፕሮጀክት ስላለ ከአንድ ስድስት አመት በኋላ ጥሩ የሆኑ ታዳጊዎች ይመጣሉ ብዬ አስባለው። የድሬ ህዝብ እግር ኳስ የሚወድ ነው ፤  ሆኖም አንዳንዴ እንዴት የድሬደዋ ተጨዋች አታስገቡም ይላሉ?  ግን ከየት ይምጣ ነው መልሱ፡፡ ፕሪምየር ሊጉን መጥነው መጫወት የማይችሉ ተጨዋቾች ናቸው ያሉን ብለን ማሰብ አለብን።  ስለዚህ ትክክለኛ ተተኪ እስኪመጣ  ድረስ ተጨዋች ግዢ ቡድኑን እያጠናከርክ መሄድ አለብህ። ዘንድሮ እንዴት ከመውረድ እንደዳንን አይተነዋል።  ስለሆነም አሁን በፕሮጀክት እየተሰራ ነው ትክክለኛ ተተኪ እስከምናገኝ ድረስ ቡድኑ ከሚወርድ በግዢ ቡድኑን አጠናክረህ ወደ ፊት ታዳጊዎችን የምትተካ መሆን አለበት። ሀዋሳን ምሳሌ አድርግ ፤ በየአመቱ አምስት ተጫዋቾች ከታች  ያሳድጋሉ፡፡ እኛም ወደፊት እንዲህ ማድረግ አለብን።

በእናተ ዘመን ድሬደዋ ላይ የሞቅ የእግር ኳስ ማዕከል ነበረች። በተለይ በሁለቱ ቡድኖች (በባቡር እና በጨርቃጨርቅ) መካከል የነበረው እንቅስቃሴ ፣ የደርቢ ድባብ እና የመሳሰሉት እንዴት ታስታውሰዋለህ ?

እውነት ለመናገር እኔ በነበርኩበት ዘመን አሁን እንዳለው በርካታ ደጋፊ ተገኝቶ ጨዋታዎችን አይመለከትም፡፡ ሆኖም ምድር ባቡር እና ጨርቃጨርቅ ሲጫወቱ ደርቢ ነበር፡፡ ልክ እንደ ቡና እና ጊዮርጊስ ጨዋታ ነበር፡፡ ጥላ ፎቁ እንኳ ባቡር ትሪፕ እና ኮተን ትሪፕ ይባል ነበር። በጣም የሚገርም ስሜት ነበረው፡፡ የዛ ዘመን የነበረው  ድባብ አሁን በዚህ ዘመን መመለስ ይከብዳል። ጨዋታው ነገ የሚደረግ ከሆነ በቃ እንቅልፍ አንተኛም ፣ ከቤት አንወጣም ፣ እራሳችንን እንጠብቅ ነበር። ጨዋታው ላይም ሁሌ ጎል አስቆጥርባቸዋለው፡፡ ከተሸነፍን ደግሞ ተወው በቃ በንዴት እንቅልፍ አንተኛም ነበር። የሆነ ወቅት ከጨርቃጨርቅ ጋር ስንጫወት የዋንጫ ጨዋታ ልዩ ዝግጅት ተደርጎ ድምፃዊት ቻቺ ታደሰ መጥታ ነበር፡፡ ሁለት የሚገርም ጎል አስቆጥሬ ዋንጫ ስናሸንፍ ሜዳ ላይ በእሷ ሙዚቃ ጨፍሬ ነበር። እንዲያውም የጨርቃጨርቅ አሰልጣኝ ጌታቸው ወልዴ ከእኛ ጋር በመጨፈሩ ከአሰልጣኝነቱ ተባሮ እንደነበረ አስታውሳለው።

በተጨዋችነት ዘመንህ የሚፈትንህ ተከላካይ ወይም ቡድን ማነው ?

በዛን ዘመን ላይ አስቸጋሪ የምላቸው ተከላካዮች ጉልበት ተክለ ሰውነት ያላቸው ሳይሆኑ በጣም ብልጥ የሆኑ ተከላካዮች የነበሩት አንዋር ሲራጅ እና ሳሙኤል ደምሴ ነበሩ፡፡ ጉልበት እና አቅም የላቸውም ግን የበሰሉ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ አይጋፉሁም ፤ አንተ ይዘህ የምትመጣውን ኳስ በሚገርም ታይሚንግ ያበላሹብሀል ፤ ሁለቱ በጣም ያስቸግሩኝ ነበር። በጣም የማደቃቸው ተጨዋቾች ናቸው።

በ1994 ዮርዳኖስ በ3 ጎል ልዮነት እየመራህ በመጨረሻ ጨዋታ ዮርዳኖስ 4 ጎል አስቆጥሮ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ያጣህበትን ወቅት እንዴት ታስታውሰዋለህ? በወቅቱ ስለተወራው የመላቀቅ ወሬስ ምን ትላለህ?

አዎ የዛን ሰአት እኔ እና እርሱ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ነበርን፡፡ እኔ በሦስት ጎል እቀድመው ነበር ፤ እሱ መብራት ኃይል ሆኖ ከ ጊዮርጊስ ጋር ነበር  ይጫወት የነበረው። እኔ ደግሞ ከባቡር ጋር ሆኜ መቀለ ላይ ከትራንስ ጋር ነበር በእኩል ሰአት እየተጫወትን ነበረው። ታዲያ አንዲት ጋዜጠኛ ነች ጨዋታው ሳይጠናቀቅ ውጤቱን ሳይሆን እኔ ሦስት ጎል ማስቆጠሬን ስሜን ጠቅሳ አአ ስታድየም ስትናገር ትራንሶች ለቀውለታል ብለው ጊዮርጊሶች ደግሞ አምስት ጎል ለቀውለታል ተብሏል። እንግዲህ በዛ ይመስለኛል መላቀቁ ሊመጣ የቻለው። ጋዜጠኛዋ ትክክል አልሰራችም ነበር የጎላ ስህተት ነው የሰራችው፡፡ ጨዋታ ሳያልቅ በወቅቱ ውጤት ብቻ ብትገልፅ ጥሩ ነበር ያው ይህ ነገር ተፈጠረ።  ምንም አልተሰማኝም ሁለታችንም ድሬደዋ ልጆች ስለ ሆንን ብዙም አልተሰማኝም። እንዲያውም በኢትዮዽያ እግር ኳስ በዚያ ዘመን ኮከብ ጎል አስቆጣሪ የምንሆነው አሰግድ ተስፋዬ ፣ ዮርዳኖስ አባይ ፣ ስምኦን አባይ እና እኔ ነበርኩ፡፡ ይገርምሀል ዛሬ ለድሬደዋ ጎል የሚያስቆጥር አይደለም ወደ ጎል የሚደርስ አጥቂ ጠፋ፡፡

በዚህ ዘመን በጣም የምታደንቀው አጥቂ ማነው ?

አይ በዚህ ዘመን አይን የሚገባ አጥቂ አለ ብዬ አላስብም፡፡ ለምን መሰለህ ወጥ የሆነ አቋም የላቸውም ይዋዥቃሉ፡፡ ዛሬ ጎል አስቆጥረው በደጋፊ ተጨፍሮላቸው በሳምንቱ በደጋፊ ‘ይሄን ልጅ ቀይረው’ ሲበል ትሰማለህ። ስለዚህ በራስ መተማመን የላቸውም ድንጉጦች ናቸው፡፡ ሳጥን ውስጥ ኳስ አግኝተው ቶሎ ፈርተው ከእግራቸው እንዲወጣ ብቻ በመምታት ያመክኑታል፡፡ በእኔ አስተያየት ተጋኖ የማደንቀው አጥቂ የለም ባይ ነኝ፡፡

ቀረ የምትለው የምታስተላልፈው መልክት ካለ ?

ያው አሁን ባለው የድሬዳዋ ከተማ እግርኳስ ክለብ ላይ የህዝቡ ፍላጎት ውጤት ላይ ነው። የድሬዳዋ ህዝብ ትግስተኛ ነው ፤ አንድ ነገር ለመስራት ደግሞ ትዕግስትና ጊዜ ያስፈልጋል። አንድ አሰልጣኝ በአንድ አመት ውስጥ ውጤት ማምጣት ይከብዳል ፣ አንድ ሁለት ሦስት አመት እያለ ቡድኑን እያስተካከለ ውጤት እያመጣ ይሄዳል እንጂ በአንዴ የሚሆን ነገር የለም፡፡ ስለዚህ በትዕግስት ከአሰልጣኙ እና ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን ቡድኑን በመደገፍ ወደ ፊት እንዲሄድ ማድረግ አለባቸው ።

በመጨረሻም አሰግድ ተስፈዬ በጣም የማከብረውና የምወደው ሁሌም ከጎኔ በመሆን የሚመክረኝ ጥሩ ደረጃ እንድደርስ ያደረገኝ  ወንድሜ ነው እና በዚህ አጋጣሚ ፈጣሪ ነፍሱን በገነት ያኑረው እላለው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *