በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ጉልህ ስፍራ ከሚሰጣቸው ኢትዮጵያዊያን መካከል አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ ግንባር ቀደሙ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ራዲዮ እና የተለያዩ የሃገር ውስጥ የህትመት ውጤቶች ስለሃገር ውስጥ ስፖርት መዘገብ የጀመሩት አቶ ፍቅሩ በ1957 እ.ኤ.አ. በሱዳን እና ኢትዮጵያ መካከል የተደረገውን ጨዋታ በቀጥታ በሬዲዮ ማስተላለፍ የቻሉ የመጀመሪያው የስፖርት ጋዜጠኛ ናቸው፡፡
አቶ ፍቅሩ የኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር በ1968 እ.ኤ.አ. ሲመሰረት የመጀመሪያው ፕሬዝደንት የነበሩ ሲሆን በብስክሌት ፌድሬሽን፣ ቴኒስ ፌድሬሽን እና የኦሎምፒክ ኮሚቴ በዋና ፀሃፊነት፣ በእግርኳስ ፌድሬሽን የህዝብ ግንኙነት በመሆን ሃገራቸውን አገልግለዋል፡፡ በዓለማቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እና የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ውስጥም በአመራርነት ፣ የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) የቀድሞ ፕሬዝደንት የነበሩት የኢሳ ሃያቱ አማካሪ ጭምር የነበሩ ታላቅ የስፖርት ሰው ነበሩ፡፡
ከ1976 እ.ኤ.አ ጀምሮ ኑሯቸውን በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ያደረጉት አቶ ፍቅሩ ለለኪፕ፣ ፉትቦል ፍራንስ፣ ዶቼቬሌ (የጀርመን ድምፅ) እና ሌሎች የአለማቀፍ ታዋቂ መገናኛ ብዙሃን መስራት ከመቻላቸውም በተጨማሪ “የፒያሳ ልጅ” የተሰኘ ግሩም መፅሀፍ አበርክተዋል፡፡
አቶ ፍቅሩ በጣሊያን መዲና ሮም ላይ የኢትዮጵያዊያን ስፖርት እና ባህል ምክርቤት በአውሮፓ የሚያዘጋጀው አመታዊ ውድድር እና አቡጃ ናይጄሪያ ላይ ከሚደረገው የአፍሪካ ኦሎምፒክ ኮሚቴ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ከማቅናታቸው በፊት ባሳለፍነው ሳምንት ካፍ ስለወሰዳቸው ስርነቀል ለውጦች እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ ከሚካሄድበት ከጥር ወር ወደ ሰኔ ተዛውሯል፡፡ የተሳታፊ ሃገራትም ወደ 24 አድጓል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ ያለዎት ምልከታ ምን ይመስላል?
አፍሪካዊያን ተጫዋቾችን ቀጥረው የሚያጫውቱ የአውሮፓ ክለቦች ሁሌም በጥር/የካቲት ወር ተጫዋቾቻቸው በአፍሪካ ዋንጫው ምክንያት መልቀቅ አይፈልጉም ነበር፡፡ የሚፈልጉት ተጫዋቾቻቸው በአውሮፓዊያን የእረፍት ግዜ ሰኔ/ሐምሌ ላይ ለየሃገሮቻቸው እንዲጫወቱ ነበር፡፡ አዲሱ የካፍ ማዳጋስካራዊው ፕሬዝደንት አህመድ ለአውሮፓዊያን እና ለፊፋ በጣም ቅርብ ነው፡፡ ስለዚህም አውሮፓዊያኑን ለማስደሰት የአፍሪካ ዋንጫ የሚካሄድበትን ወቅት ቀይሮታል፡፡ ሁሉም ሰው በተለይ ኢትዮጵያዊያን ሰኔ/ሐምሌ የዝናብ ወቅት እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ እንዴት ኢትዮጵያ ውድድሩን በዝናብ ወቅት ማስተናገድ ትችላለች? ወይ ውድድሩን አዳማ እና ድሬዳዋ ለማስተናገድ ካልወሰንን በቀር፡፡ ውሳኔው በጣም መጥፎ ነው፡፡
የተሳታፊ ሃገራትን ቁጥር ከ16 ወደ 24 መጨመሩም ትክክለኛ ውሳኔ አይደለም፡፡ አፍሪካ ድሃ አህጉር ናት፡፡ በጣም ውስን ሃገራት ናቸው 24 ሃገራትን የሚያሳትፍ ውድድር የማዘጋጀት ብቃት እና የመሰረተ ልማት ያላቸው፡፡ ቢያንስ 6 ስታዲየሞች፣ 12 የልምምድ ሜዳዎች፣ ለ24ቱም ቡድኖች የሚሆን የሆቴል አቅርቦት፣ ለዳኞች የሚሆን ስፍራ እና የመሳሰሉት ቢያንስ በተለያዩ ከተሞች ያስፈልጋሉ፡፡ እንደውም 16 ቡድኖች በሚካፈሉበት የአፍሪካ ዋንጫ እንኳን ከዝግጅት ጋር ተያይዞ ብዙ ችግሮች ታይተውበታል፡፡ የአየር ትራንስፖርት ያስፈልጋል ፤ ከዚህ ሁሉ ግን 24 ጠንካራ ተፎካካሪ የሆኑ ሃገራትን ማግኘት ይቸግራል፡፡ ምንአልባት አዲሱ የካፍ ፕሬዝደንት እንደማዳጋስካር እና ጅቡቲ ያሉ ሃገራት ወደ አፍሪካው ዋንጫው አንድ ቀን የማለፍ ተስፋ ይኖራቸዋል ብሎ ጠብቆ ይሆናል፡፡ የውድድሩ ጥራት እጅግ በጣም የወረደ ነው የሚሆነው፡፡ ተሳታፊዎችን ወደ 24 ያሳደገችው አውሮፓ እንኳን የእግርኳሱን ጥራት ለማምጣት እየተቸገረች ነው፡፡
ካሜሩን ውድድሩን ለማስተናገድ ቃል የገባችው በ16 ሃገራት ነበር፡፡ የተሳታፊ ሃገራት ቁጥርን እንደዚሁ ዝም ብለህ አትጨምርም፡፡ ፊፋ የዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ሃገራትን ወደ 48 ከፍ አድርጓል ግን ከ2026 ጀምሮ ነው፡፡ በ2018 ወይም በ2022 አይደለም፡፡ አፍሪካ ውስጥ ብቻ ነው እንደዚህ አይነት ለውጦችን ልትጠብቅ የምትችለው፡፡
የአፍሪካ እግርኳስ ያለመንግስታት ድጋፍ በህይወት ሊቆይ አይችልም፡፡ አንድ ሃገር ያለመንግስት የገንዘብ እርዳታ የአፍሪካ ዋንጫን ሊያስተናግድ አይችልም፡፡ በዛው ልክም እውነታውን ማወቅ አለብን ፤ የአፍሪካ መንግስታት ከእግርኳስ በላይ አሳሳቢ ጉዳዮች አሉባቸው፡፡ በአንድ ጀንበር ተነስተን ሁሉንም ነገር መለወጥ አንችልም፡፡
የካፍ ፕሬዝደንት አህመድ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ የወሰዱት እርምጃዎች የኢሳ ሃያቱን ስራዎች መሬት ለመቅበር ነው የሚሉ ሃሳቦች ይነሳሉ፡፡ እርሶ በዚህ ሃሳብ ይስማማሉ?
የካፍ ፕሬዝደንት አህመድ ከቀድሞ ፕሬዝደንት ሃያቱ ጋር እኩል ለመሆን በጣም እየጣረ ነው፡፡ እሱ (አህመድ) ማለት ልክ እንደአፍሪካ መንግስታት ከእነሱ በፊት የነበሩት የቀድሞ ስርዓት ምንም እንዳልሰራ እና አዲሱ መንግስት ግን የተሻለ እንደሚሰራ ለማረጋገጥ እንደሚሞክሩት በአህጉሪቱ ያሉት መንግስታት አይነት ነው፡፡ አህመድ የ2019 የአፍሪካ ዋንጫ በፕሬዝደንታዊው ምርጫ ግዜ ለረዳችው ሞሮኮ የማስተናገዱ እድል እንዲሰጣት ፅኑ ፍላጎት አለው፡፡ የሞሮኮ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት (ፋውዚ ሌካ) ደንቡን በማሻሻል ሶስተኛ የካፍ ምክትል ፕሬዝደንት አድርጎ ሾሟል፡፡ ለ60 ዓመታት ሁለት ምክትል ፕሬዝደንቶች ብቻ ነበሩ፡፡
በካፍ ከተወሰዱት ሌሎች ለውጦች መካከል ለፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩ እጩዎችን ከ70 ዓመት ያልበለጡ እንዲሆኑ የሚያስገድድ ህግ ነው፡፡ ሌሎች ለውጦችን እና የተወሰኑ ውሳኔዎችን እንዴት ተመለከቱት?
አህመድ አብዛኞቹን ደጋፊዎቹን በተለያዩ የስልጣን እርከኖች ላይ በመሾም አስደስቷል፡፡ እኔ የተስሟሟሁባቸው ሁለት ውሳኔዎች የእድሜ መጠኑን ከ70 እንዳይበልጥ መገደቡ እና የዛንዚባር ከካፍ አባልነት መሰረዟ ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ጉዳዮችን ስለምደግፍ ለረጅም ግዜ ስከራከርባቸው ነበር፡፡ ሌላው አፍሪካን ወክለው በፊፋ ካውንስል ውስጥ ያሉ ሰዎችን ወደ የካፍ ስራ አሰፃሚ አባል መደረጋቸው የሚደገፍ ሃሳብ ነው፡፡
ካፍ ዛንዚባርን ከአባልነት ከአራት ወር በኃላ መሰረዙን ደግፈዋል፡፡ ቢሆንም እንደፌሬ ደሴቶች (ዴንማርክ) እና ጂብራልታር (ዩናይትድ ኪንግደም) ያሉ በሌሎች ሃገራት ስር ያሉ የራስ-ገዝ አስተዳደሮች የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ሙሉ አባል ስለሆኑ በውድድሮች ላይ ይሳተፋሉ፡፡ የዛንዚባር የአባልነት ጥያቄ ከነዚህ የራስ-ገዝ አስተዳደሮች ምን የሚለየው ነገር አለ? የዛንዚባር ክለቦች ለረጅም ግዜያት በአፍሪካ የክለቦች ውድድር እየተሳተፉ እንደሚገኙ እየታወቀ ዛንዚባርን ለምን አባል ለማድረግ አልተፈለገም?
ልክ ነህ፡፡ አንዳንድ ግዛቶች በፊፋ እውቅና አላቸው፡፡ ለዛም ነው ታንዛኒያ የዛንዚባርን የአባልነት ጥያቄ የደገፈችው፡፡ ከግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን ነገር አስቀድሞም ዛንዚባር ልክ እንደታንጋኒካ ሁሉ ነፃ ሃገር ነበረች፡፡ አንድ ላይ ታንዛኒያ ከመሆናቸው በፊትም ሁሉ ነፃ ሃገር ነበረች፡፡ እንደ ቤርሙዳ፣ ታሂቲ ያሉ ሃገራት በፈረንሳይ፣ ብሪታንያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ስር ናቸው፡፡ እንደ ቻይና፣ ሆንግ ኮንግ እና ቴፒ ያሉትም አሉ፡፡ ከአሁን በኃላ የፊፋ አባል ለመሆን በተባበሩት መንግስታት እውቅና ሊሰጥህ ይገባል፡፡ ይህ ደግሞ አባል ከመሆን በፊት ነው፡፡ ይህ የዛንዚባር ጉዳይ ብቻ አይደለም ሪዩኒየን ደሴቶች በካፍ እውቅና ተሰጧታል፡፡ ግን ይህ ፈፅሞ ስህተት ነው፡፡ አህመድ በሪዩኒየን ጉዳይ ላይ ጥያቄ አያነሳም፡፡ ምክንያቱም ሪዩኒየን የማዳጋስካር ጎረቤት ስለሆነች ነው፡፡
በመጋቢት በነበረው የካፍ ፕሬዝደንታዊ እና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫ ላይ የፊፋው ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ አህመድ አህመድ እንዲመረጡ የተቻላቸውን አድርገዋል የሚሉ በርካታ ናቸው፡፡ አሁን ላይ የወሰኑት ስርነቀል ለውጦችም ከኢንፋንቲኖ ጋር በተዘዋዋሪ ይያያዛሉ፡፡ እርሶ ኢንፋንቲኖ በካፍ ውስጣዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ ይገባሉ ብለው ያምናሉ?
አዎ፡፡ ኢንፋንቲኖ ከሃያቱ ድጋፍ ስላላገኘ በሃያቱ ላይ ዘመቻ ከፍቶ ነበር፡፡ ይህን ለማረጋገጥ አንድ ኮንጓዊ የኢንፋንቲኖን መጥፎ ስራዎች ሲያስፈፅም እንደነበር ይታወቃል፡፡ አዲስ አበባ ላይ ከጠቅላላ ጉባኤው በፊት ፊፋ፣ ግብፅ እና ሞሮኮ ድምፅ ሰጪዎችን በገንዘብ ሲበክሉ ሂልተን ሆቴል የታየ ነው፡፡ ይህ በአፍሪካ የተለመደ አይነተኛ አሰራር ነው፡፡ ባለብን ድህነት ምክንያት የምርጫ ድምፅን በገንዘብ መሸጥ የተለመደ ነው፡፡ በእኔ ግዜ የነበረን ብቸኛ ሃብት ክብራችን ነበር፡፡ ይህ ሃብት ነው አሁንም ድረስ ያለኝ፡፡
መጋቢት ላይ ካፍ ባዘጋጀው የአፍሪካ እግርኳስ ፎረም ላይ የአፍሪካ መንግስታት ለወጣቶች ስፖርት የሰጡት ግምት አነስተኛ መሆኑን አፅኖት ሰጥተው ሲናገሩ አስተውለናል፡፡ ይህ ችግር በቅርብ አመታት ውስጥ ይፈታል ብለው ያስባሉ?
አፍሪካ አሁን ባለን አያያዝ በወጣቶቿ ላይ ኢንቨስት የምታደርግ አይመስለኝም፡፡ የእኛን ሃገር ስፖርት ተመልከት ፤ ለምሳሌ የትምህርት ቤቶችን ውድድር ዳግም እስካልመለስን ድረስ እየጠፋን ነው የምንሄደው፡፡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ የለም፣ የተደራጀ ክለብ የለም፡፡ ግን ቱሪስቶች አሉን በየሄዱበት ያልሆነ ፕሮፖጋንዳቸውን የሚነዙ፡፡ የቦውሊንግ፣ ውሃ ዋና፣ ጅምናስቲክ፣ ቅርጫት ኳስ የመሳሰሉት የኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ ነገር ግን ስለነዚህ ስፖርቶች ተዘግቦም ተሰርቶም አይታወቅም፡፡ ይህ ወጣቶችን የማይጠቅም አካሄድ ነው አፍሪካ እየተከተለች ያለችው፡፡ ይህ በጣም ያሳዝናል፡፡