በሶከር ኢትዮጵያ ​የከፍተኛ ሊግ የውድድር አመቱ ምርጥ 11

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ሐምሌ 12 በተደረገው የፍፃሜ ጨዋታ መጠናቀቁ የሚታወስ ነው፡፡ ሶከር ኢትዮጵያም በውድድር አመቱ በቦታቸው ምርጥ አቋም ያሳዩ 11 ተጫዋቾችን መርጣለች፡፡

ግብ ጠባቂ

በረከት አማረ – ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ

ከፍተኛ ሊጉን በ2ኛነት አጠናቆ ወደ ፕሪምየር ሊግ ላደገው ወልዋሎ በረከት ያበረከተው አስተዋጽኦ ጎልቶ የሚጠቀስ ነው፡፡ ቡድኑ በሚቸገርባቸው ጨዋታዎች ላይ በረከት ድንቅ አቋሙን በማሳየት ክለቡን ሲታደግ በተደጋጋሚ ተስተውሏል፡፡


ተከላካዮች


ይትባረክ ሐብታሙ – ሻሸመኔ ከተማ

ሻሻመኔ ከተማ የሚያደርገው የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚጀምረው ከቀኝ መስመር ተከላካዩ ይትባረክ ነው፡፡ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ለማደግ እስከ መጨረሻዎቹ ሳምንታት ድረስ ባደረገው ትግል ውስጥም ቁልፍ ሚና መጫወት የቻለ ተጫዋች ነው፡፡

ኤፍሬም ጌታቸው – ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ

ከደደቢት በውሰት የውድድር አመቱን በወልዋሎ ያሳለፈው ኤፍሬም አመቱን ሙሉ ያለማቆረጥ ጨዋታ ከማድረጉ በተጨማሪ ወጥ አቋም በማሳየትም ከሊጉ ተጫዋቾች የተሻለ ነው፡፡


አሌክስ ተሰማ – መቀለ ከተማ

የቀድሞው የዳሽን ቢራ እና ሀዋሳ ከተማ ተከላካይ ለመቀለ ከተማ የተከላካይ መስመር ጥንካሬ ቁልፍ ነበር፡፡ ቡድኑ የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የሚተገብር እንደመሆኑ ስራ የሚበዛበትን የተከላካይ መስመር በአግባቡ በመቆጣጠር መልካም አመት አሳልፏል፡፡


ሮቤል አስራት – ጅማ ከተማ

በግራ የተከላካይ ክፍል ድንቅ አመት ያሳለፈው ሮቤል በፕሪምየር ሊጉ ክለቦች አይን እንዲያርፍበት ያደረገውን እንቅስቃሴ አሳይቷል፡፡ ከፊቱ ከሚገኙ ተጫዋቾች ጋር ያለው መናበብም ድንቅ ነው፡፡


አማካዮች


ሚኪያስ ግርማ – ባህርዳር ከተማ

ባህር ዳር ከተማ እና አራዳ ክፍለ ከተማ በከፍተኛ ሊጉ ጥሩ አመት ባያሳልፉም በሁለቱም ክለቦች ሚኪያስ ግርማ በግሉ ጥሩ የውድድር አመት አሳልፏል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች መሰለፍ የሚችለው ሚኪያስ ሜዳ አካሎ የመጫወት ታታሪነቱ ልዩ መለያው ነው፡፡


መኩሪያ ደሱ – ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ

መኩርያ ከአማካይ ክፍል እየተነሳ የሚያስቆጥራቸው ጎሎች ለወልዋሎ ውጤታማነት ቁልፍ ነበሩ፡፡ ከርቀት በሚመታቸው ኳሶች ፣ ኳስን በቀላሉ በመንጠቅ እና በእርጋታ በማሰራጨት የተካነው መኩርያ አመቱን ሙሉ ወጥ አቋም ማሳየት ችሏል፡፡


መጣባቸው ሙሉ – ጅማ ከተማ

ከፋሲል ከተማ በውሰት ወደ ጅማ ያመራው መጣባቸው ጅማ የመሀል ክፍሉን ተቆጣጥሮ እንዲጫወት ወሳኝ ሚናን ተወጥቷል፡፡ ለአጥቂዎች የሚያቀብላቸው የተመጠኑ ኳሶችም ቡድኑ ውጤታማ እንዲሆን አግዞታል፡፡


አጥቂዎች


አማኑኤል ገብረሚካኤል – መቀለ ከተማ

በከፍተኛ ሊጉ ዘንድሮ እንደአማኑኤል ገብረሚካኤል ትኩረት የሳበ ተጫዋች የለም፡፡ በወሳኝ ሰአት የሚያስቆጥራቸው ጎሎች ባይኖሩ መቀለ ለፕሪምየር ሊጉ ባልበቃ ነበር፡፡ በፍጹም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ ያለው እርጋታ እና የመጨረስ ብቃት በቀጣይ አመል በፕሪምየር ሊጉ ለመመልከት የሚያጓጓ ነው፡፡

ዘካርያስ ፍቅሬ – ሀላባ ከተማ

የከፍተኛውን ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ያጠናቀቀው ዘካርያስ ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ባያድግም ወደ ድሬዳዋ ከተማ በማምራቱ በቀጣይ አመት በሊጉ እንመለከተዋለን፡፡ ፈጣን እና ቦታ በመቀያየር የተከላካይ ክፍል መረበሽ የሚችል አጥቂም ነው፡፡

እንዳለ ደባልቄ – ሀዲያ ሆሳዕና

ፈጣንና ጉልበት የተቀላቀለበት አጨዋወቱ ለተከላካዮች ራስ ምታት የሆነው ፈርጣማው እንዳለ ቡድኑ በጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ባይገኝ እንኳን በግል ጥረቱ ወጀ ውስጥ በመግባት የሚያስቆጥራቸው ግቦች እና የሚፈጥራቸው የጎል እድሎች ለሀዲያ ጉዞ ወሳኝ ነበሩ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *