​የክልል ክለቦች ሻምፒዮና የመጀመርያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ቅዳሜ በደማቅ የመክፈቻ ስነ–ስርአት ሲጀመር በእለቱም 4 ጨዋታዎች ተከናውነዋል፡፡

የምድብ ለ ጨዋታዎች ረፋዱ ላይ ቢጀመሩም በይፋ የመክፈቻ ስነስርአት የተደረገው ግን በአዲሱ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ ስታድየም ከ7:30 ጀምሮ ነው፡፡ ተወዳዳሪ ክለቦች ራሳቸውን እያስተዋወቁ የማለፍ እና የወልድያ አካባቢ የባህል ውዝዋዜ ቡድን ለእንግዶች ትርኢት በማቅረብ በተጀመረው ፕሮግራም የወልድያ ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መለሰ የመክፈቻ ንግግር ካደረጉ ቡኋላ ወድድሩን በይፋ አስጀምረዋል።

ከመክፈቻው ጨዋታ በፊት ረፋድ ላይ በመልካ ቆሌ ሜዳ በተካሄደ የምድብ ለ ጨዋታ ቡሬ ከተማ ከመርካቶ አካባቢ ያለግብ በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቁ ድሬዳዋ ኮተን ከቤንች ማጂ ፖሊስ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ጨዋታቸውን ፈፅመዋል፡፡

በመሀመድ ሁሴን አላሙዲ ስታድየም በተደረገው ይፋዊ የመክፈቻ ጨዋታ ይፋዊ ወልድያ የጁ ፍሬ ሾኔ ከተማን 2-0 አሸንፏል፡፡ የከተማው ከንቲባ አቶ ሞላ መለሰ ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ጁነይዲ ባሻ እና ሌሎች የፌዴሬሽን ኃላፊዎች ተጫዋቾችን ከተዋወቁ በኋላ በጀመረው ጨዋታ ጅማሮ ጥሩ በመንቀሳቀስ እንዲሁም የግብ ሙከራ በማድረግ የተሻሉ የነበሩት ሾኔ ቢሆኑም የኋላ ኋላ ወደ ጨዋታው የገቡት ወልድያዎች ከእረፍት መልስ በ49ኛው ሮቤል ቴዎድሮስ ከግብ ጠባቂው የተመለሰውን ኳስ በመጠቀም የመጀመርያውን ጎል አስቆጥሯል፡፡ በ78ኛው ደቂቃ ደግሞ ጀማል ያሲን ከሳጥን ውጭ በማራኪ ሁኔታ አክርሮ በመምታት የወልድያን መሪነት ወደ 2-0 አሳድጎ ጨዋታው በየጁ ፍሬ ወልድያ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በመቀጠል በ11:00 በተደረገው ጨዋታ ሽረ እንዳስላሴ ቢ ያሶ ከተማን 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፏል፡፡

ያሶ ከተማ በ2ኛው ደቂቃ የዘለቀ ወረኬ ግብ ቀዳሚ መሆን ቢችሉም ሙሉ የጨዋታ የበላይነት የነበራቸው ሽረዎች የአቻነቷን ግብ በ25ኛው ደቂቃ በሸሻይ ኪዳነ አማካኘነት አስቆጥረዋል፡፡ ሽሻይ በድጋሚ በ76ኛው ደቂቃ ሽረን ወደ መሪነት ሲያሸጋግር ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ አቤል ፀጋየ ሶስተኛውን ፣ በ90ኛው ደቂቃ ደግሞ ክፍሎም ገ/ህይወት የማሳረጊያውን ጎል አስቆጥሯል።


ውድድሩ ዛሬም የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ይህን ሊንክ ተጭነው ሙሉውን መርሀ ግብር ፣ ውጤት እና ሰንጠረዥ ያገኛሉ፡-  የክልል ክለቦች ሻምፒዮና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *