​መቐለ ከተማ የ16 ተጫዋቾቹን ውል ሲያድስ ሙሴ ዮሀንስን አስፈርሟል

በ2010 የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ተሳታፊ የሚሆነው  መቐለ ከተማ የ16 ተጫዋቾችን ውል ሲያድስ ሶስት ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡

አንተነህ ገብረክርስቶስ እና ዳንኤል አድሀኖምን ያስፈረመው መቐለ የውድድር አመቱን በወሎ ኮምቦልቻ ያሳለፈው ግብ ጠባቂው ሙሴ ዮሀንስን 3ኛ የክለቡ ፈራሚ ሲያደርግ ራሱን ለቀጣይ አመት ውድድር አጠናክሮ ለመቅረብ ይረዳው ዘንድ ተጫዋቾችን የማስፈረም እንቅስቃሴ እንደሚቀጥል አሰልጣኝ ጌታቸው ዳዊት ለሶከር ኢትዮዽያ ገልፀዋል።


” ቀዳሚ ስራችን ያደረግነው ክለባችን በዘንድሮ አመት በከፍተኛ ሊጉ በነበረን ተሳትፎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንድንገባ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ተጨዋቾችን በክለቡ ለማቆየት ነው፡፡ በዚህም መሰረት የ16 ተጨዋቾችን ውል በማደስ በክለቡ ጋር እንዲቆዩ አድርገናል። በቀጣይ ቀናትም አዲስ አበባ በመምጣት ተጨማሪ የሀገር ውስጥም ሆነ የውጭ ተጨዋቾችን በማስፈረም ክለቡን ለማጠናከር ሰፊ ስራ እንሰራለን፡፡” ብለዋል፡፡
የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች የሆኑት አጥቂው አማኑኤል ገብረሚካኤል እንዲሁም ተከላካዩ አሌክስ ተሰማ ውላቸውን ካደሱ ተጫዋቾች መካከል እንደሆኑ ታውቋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *