​የክልል ክለቦች ሻምፒዮና 2ኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በወልድያ መካሄዱን ቀጥሏል፡፡ በዛሬው እለትም በሶስት ሜዳዎች 8 ጨዋታዎች ተደርገው ሻሾጎ ፣ መርሳ ፣ ሐረር ፖሊስ እና ሺንሺቾ ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈዋል፡፡


ምድብ 5

የዚህ ምድብ ጨዋታዎች በአዲሱ ሼህ መሀመድ አላሙዲ ስታድየም ነበር የተካሄዱት፡፡ በ8:00 በተካሄደው የመርሳ ከተማ እና ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ጨዋታ የመርሳ ከተማ ከወልድያ በቅርብ ርቀት በመገኘቷ ቁጥራቸው በርከት ያሉ የመረሳ ደጋፊዎች ተገኝተው ለቡድናቸው ድጋፍ ሰጥተዋል።

የእንቅስቃሴ የበላይነት የነበራቸው መርሳዎች በ25ኛው ደቂቃ ያገኙትን ፍፁም ቅጣት ምት በዘይኑ ሽፈራው አማካኝነት አስቆጥረው ቀዳሚ መሆን ሲችሉ በ45ኛው ደቂቃ ከመሀል ሜዳ ክብ መስመር አካባቢ ሀረማያዎች ያገኙትን ቅጣት ምት ሮቤል ግዛቸው አክርሮ በምታት የመርሳ ግብ ጠባቂ ስህተት ታክሎበት በአቻ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ በ61ኛው ደቂቃ ከሳጥን አካባቢ የተገኘውን ቅጣት ምት አምበሉ ንጉሴ ገመዳ አስቆጥሮ ሀረማያዎች ወደ መሪነት መሸጋገር ችለዋል።
ከጎሉ መቆጠር በኋላ ጫናቸውን ያጠናከሩት መርሳዎች 70ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ በከድር ሀሰን አማካኝነት ወደ ግብነት ቀይረው አቻ ሆነዋል። በ90 ደቂቃ ደግሞ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ዘይኑ ሽፈራው አስቆጥሮ ጨዋታው በመርሳ ከተማ 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በዚሁ ስታድየም በተካሄደው ሁለተኛ ጨዋታ ሻሾጎ ከተማ አላማጣ ከተማን 3-0 አሸንፏል፡፡ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ እና አነስተኛ የግብ ሙከራ በተስተናገደበት ጨዋታ በ45ኛው ደቂቃ ሻሾጎዎች አስቻለው መናሮ ባስቆጠረው ግብ ታግዘው በ1-0 መሪነት የመጀመርያውን አጋማሽ አጠናቀዋል፡፡

በ72ኛው ደቂቃ የአላማጣ ተከላካዩች የሰሩትን ስህተት በመጠቀም በጨዋታው ጥሩ ሲንቀሳቀስ የዋለው አኔቦ ሙለቱ የሻሾጎን መሪነት ከፍ ሲያደርግ በ89ኛው ደቂቃ በድጋሚ አኔቦ ሙለቱ የአጨራረስ ብቃቱን ተጠቅሞ በማስቆጠር ጨዋታው በሻሾጎ ከተማ 3-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።


ምድብ 6

የዚህ ምድብ ጨዋታዎች በመልካ ቆሌ ስታድየም የተካሄዱ ሲሆን አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ከ ገንደውሀ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ቀጥሎ በተካሄደው ጨዋታ ደግሞ ሐረር ፖሊስ ኦሮሚያ ፖሊስን 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡


ምድብ 7

በወልዲያ መምህራን ኮሌጅ የተካሄዱት የዚህ ምድብ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ነው የተጠናቀቁት፡፡ ገንፈል ውቅሮ ከ ማሺ ከተማ 1-1 አቻ ሲለያዩ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ከ ቀበሌ 07 ደግሞ ያለግብ ጨዋታቸውን አጠናቀዋል፡፡
ምድብ 8
እነንደ ምድብ 7 ሁሉ የዚህ ምድብ ጨዋታዎችም በወልዲያ መምህራን ኮሌጅ ነበር የተካሄዱት፡፡ ሺንሺቾ ከተማ አቃቂ ማዞርያን 1-0 ሲያሸንፍ ቀበሌ 06 ከ ጫንጮ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡


ውድድሩ ነገ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ይህን ሊንክ ተጭነው ሙሉውን መርሀ ግብር ፣ ውጤት እና ሰንጠረዥ ያገኛሉ፡-  የክልል ክለቦች ሻምፒዮና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *