በተጠናቀቀው የውድድር አመት የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ‘ሀ’ ምንም ሽንፈት ሳያስተናግድ በአንድ ጨዋታ ብቻ አቻ በመለያየት ማግኘት ከሚገባው 54 ነጥብ 52 ነጥቦች በመሰብሰብ ከተከታዩ አዳማ በ13 ነጥቦች ርቆ የምድቡ አሸናፊ እንዲሁም በማጠቃለያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በማሸነፍ የሊጉን ዋንጫ ለሶስተኛ ጊዜ ማሸነፍ የቻለው ደደቢት በክረምቱ የዝውውር መስኮት ቡድኑን ለማጠናከር ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
በውድድር ዘመኑ ማብቂያ ላይ ውላቸው መጠናቀቁን ተከትሎ ፍሬወይኒ ገብሩ እና ገነት አሰግድ ክለቡን መልቀቃቸውን ተከትሎ ሊፈጠር የሚችለውን ክፍተት ለመድፈን በዛሬው እለት ክለቡ ሁለት ግብ ጠባቂዎችን ማስፈረሙን አሳውቋል፡፡
በአዲስአበባ ከተማ የተሳካ ቆይታን ማሳለፍ የቻለችው ስርጉት ተስፋዬ ከአንድ አመት ቆይታ በኃላ ዳግም ሰማያዊዎቹን በሁለት አመት ኮንትራት ተቀላቅላለች፡፡ የቀድሞዋ የቅዱስ ጊዮርጊስ ግብ ጠባቂ እንዲሁም በውድድር ዘመኑ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እምብዛም የመጫወት እድል ያላገኘችው ገነት አክሊሉ በተመሳሳይ ቡድኑን በአንድ አመት ውል ተቀላቅላለች፡፡
በተያያዘ ዜና በክለቡ ውላቸው ከተጠናቀቁ ተጫዋቾች መካከል ተከላካይዋ ዘቢብ ኃይለስላሴ እና አማካይዋ ብርቱካን ገብረክርስቶስ በቀጣይ በክለቡ ለመቆየት ከክለቡ ጋር የተስማሙ ሲሆን በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት አዲስ ውል እንደሚፈርሙ ይጠበቃል፡፡ በተቃራኒው በተደጋጋሚ ጉዳቶች ክለቡን ማገልገል ያልቻለችው ተከላካይዋ ውብአለም ፀጋዬ ክለቡን ለመልቀቅ መቃረቧ ታውቋል፡፡
ደደቢት በቀጣዮቹ ቀናት ቡድኑ ተጨማሪ አዳዲስ ተጫዋቾችን እንደሚያስፈርም ይጠበቃል፡፡