በኬንያ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ቻን ውድድር የመጨረሻ የማጣርያ ጨዋታውን ከሱዳን ጋር የሚያደርገው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን በአዳማ ዝግጅቱን እያደረገ ይገኛል።
ብሔራዊ ቡድኑ ከጅቡቲ 5-1 ድል መልስ የተወሰኑ ቀናት እረፍት ካደረገ በኋላ ለ24 ተጨዋቾች ጥሪ በማድረግ በአዳማ ከተማ ኤክስክሉሲቭ ሆቴል ማረፊያቸው በማድረግ ዝግጅታቸውን ከጀመሩ አራተኛ ቀናቸውን አሰቀጥረዋል፡፡
በዛሬው እለት 09:30 ላይ በአዳማ በአበበ ቢቂላ ስታድየም ልምምዳቸው ለመከታተል እንደቻልነው 16 ተጨዋቾች ብቻ ተገኝተዋል፡፡ ሽመክት ጉግሳ እና አሜ መሀመድ በጉዳት ምክንያት ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለው ያልሰሩ ሲሆን ጌታነህ ከበደ ፣ አስቻለው ታመነ ፣ ሳላዲን ሰኢድ ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ሙጂብ ቃሲም በግል ጉዳይ በዛሬው ልምምድ ላይ ያልተገኙ ተጨዋቾች ናቸው። የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማካይ ምንተስኖት አዳነ እና የመከላከያው የመስመር አጥቂ ሳሙኤል ሳሊሶ በዛሬው ልምምድ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ ከቡድኑ ጋር ተቀላቅለው ልምምድ ሰርተዋል።
ለ1:30 ያህል በቆየው መርሀ ግብር ለሁለት ተከፍሎ በግማሽ ሜዳ በመጫወት ጠንከር ያለ ልምምድ ሲሰሩ ተመልክተናል። ቡድኑ የተወሰኑ ቀናት በአዳማ ቆይታ በማድረግ ዝግጅቱን አድርጎ ጨዋታው ወደሚካሄድበት ሀዋሳ ከተማ እንደሚያቀና ታውቋል፡፡ ከሱዳን ጨዋታ አስቀድሞ የአቋም መፈተሻ የወዳጅነት ጨዋታ ከአንድ ሀገር ጋር ለማድረግ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ለማወቅ ችለናል።
የቻን የመጨረሻ ዙር ማጣርያ የመጀመርያው ጨዋታ ከነሐሴ 5 እስከ 7 ድረስ ባለው ቀን በሀዋሳ ኢንተርናሽናል ስቴዲዮም የሚካሄድ ሲሆን የመልሱ ጨዋታ በሳምንቱ ሱዳን ላይ የሚካሄድ ይሆናል።