​ኡመድ ኡኩሪ ለጋምቤላ ክለቦች ድጋፍ አደረገ

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አጥቂ ኡመድ ኡኩሪ በተወለደባት ጋምቤላ ላሉ ክለቦች እሁድ እለት የመለያ ትጥቅ እና ኳሶችን ድጋፍ አድርጓል፡፡ ኡመድ ድጋፉን ያደረገው በክልሉ ለሚገኙት ጋምቤላ ዩኒቲ እና ጋምቤላ ከተማ የእግርኳስ ቡድኖች እና በፓትሪክ ኦቶንግ ኦላሚ ለሚተዳደረው የፕሮጀክት የታዳጊዎች ቡድን ነው፡፡

በግብፅ የእግርኳስ ህይወቱን እየገፋ የሚገኘው ኡመድ ድጋፉን ለማድረግ ለረጅም ግዜያት እያሰበ እንደነበር ለሶከር ኢትዮጵያ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ “እንደነዚህ አይነት ድጋፎችን ለማድረግ አስባለው፡፡ ግን በጊዜ መጣበብ ምክንያት ይህንን ማድረግ አልቻልኩም ነበር፡፡ ይህንን ድጋፍ ያደረግኩት እየደከመ ያለውን የክልሉን ስፖርት ለማነቃቃት ነው፡፡”

ኡመድ ድጋፉን መደረጉን ተከትሎ በክለቦቹ እና የፕሮጀክት ቡድኑ ላይ ጥሩ የሆነ የመነቃቃት መንፈስ እንደሚፈጠር ያምናል፡፡ “ይህ በጣም ትልቅ እገዛ አይደለም፡፡ ከማህበረሰቡ እንደመውጣቴ ለማህብረሰቡ መልሼ መስጠት አለብኝ፡፡ ከኋላ ያለፈውን መመልከት አለብኝ፡፡ ለተጫዋቾቹ ይህ የሚሰጠው የተለየ ስሜት አለ፡፡ ልጅ ሆኜ ኳስ እና ማልያ ሲሰጠኝ የተሰማኝ ስሜት አሁንም አልረሳውም፡፡ ስለዚህም ለእኚህ ልጆች የተደረገው ድጋፍ ጥሩ መነሳሺያ ይሆናቸዋል፡፡ ለወደፊቱም ጠንክረው እንዲሰሩ ያስችላል፡፡”
ኡመድ ለጋምቤላ ከተማ የመለያ ትጥቅ ሲያበረክት ለጋምቤላ ዩኒቲ የመጫወቻ ኳሶችን እና 26 መለያ ትጥቆችን አበርክቷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለፕሮጀክት ቡድኑ ከ15 እና 17 ዓመት ቡድኖች የመጫወቻ ኳሶችን እና መለያ ትጥቆችን ድጋፍ ማድረጉ ታውቋል፡፡

ኡመድ በግብፅ ፕሪምየር ሊግ በኤል ኤንታግ ኤል ሃርቢ የተሳካ ግዜን በውድድር አመቱ ማሳለፍ ችሏል፡፡ የኡመድ የብሄራዊ ቡድን አጋር የሆነው ሽመልስ በቀለ በያዝነው 2009 ለሀዋሳ ከተማ ስፖርት ክለብ በተመሳሳይ መልኩ የመለያ ትጥቅ ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡
ፎቶ በፓትሪክ ኦቶንግ ኦላሚ

1 Comment

  1. ኦመድ ኡኩሪን በ1996ዓ/ም ጋምቤላ ኮሌጅ እያለሁ አውቀዋለሁ፡፡ አብሬውም ትሬይኒንግ የመስራት አጋጣሚ አግንቼም ነበር፡፡ እሱ ታታሪ፡የማይደክም፡በዓላማ የሚንቀሳቀስ ፅኑ ልጅ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት ከእሱ የሚበልጡ፡የሚስተካከሉም ብዙ የኑዌር፡መጃንግናአኝዋ ብሔረሰብ ተወላጆች ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ የአስተዳደራዊ ችግሮች ልጆቹ በኡመድ ደረጃ ሊገኙ አልቻሉም፡፡ በተለይ በኳስ ችሎታው በትልቅ ደረጃ ሊጫወት ሲገባ ባጭር ከቀረው ኳሰኛ ማናማኚ የሚስተካከል ኳሰኛ አሁን በኢትዮ.ፕሪሜርሊግ መመልከት አልቻልኩም፡፡ ብራቮ ኡመቻ!

Leave a Reply