በነሃሴ ወር ለሚደረገው የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮና (ቻን) የመጨረሻ ዙር ጨዋታ ኢትዮጵያ ለዝግጅት እንዲረዳት ከዛምቢያ ጋር ሉሳካ ላይ የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንደምታደርግ ታውቋል፡፡
ኢትዮጵያ በቻን ማጣሪያ ሀዋሳ ላይ ሱዳንን በመካከለኛው እና ምስራቅ ዞን ስታስተናግድ ዛምቢያ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ትጫወታለች፡፡ ሁለቱም ሃገራት ከፊታቸው ላለባቸው ጨዋታ እንዲረዳቸው ነው የአቋም መለኪያ ጨዋታውን ለማድረግ የተስማሙት፡፡ ኢትዮጵያ ጅቡቲን እንዲሁም ዛምቢያ ስዋዚላንድ በቀላሉ አሸንፈው ወደ ሁለተኛው ማጣሪያ ዙር መሻገራቸውን ተከትሎ ጠንካራ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማግኘተ ሲፈልጉ እንደነበረም ተነግሯል፡፡
ዛምቢያ እና ኢትዮጵያ በሰኔ ወር በተደገረው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ መጀመሪያ ጨዋታ አስቀድሞ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ አቅደው የነበረ ቢሆን በግዜ መጣበብ ምክንያት ዛምቢያ ጨዋታውን መሰረዟ ይታወሳል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዝግጅቱን አዳማ ላይ እያደረገ ሲሆን ሐሙስ ወደ ሉሳካ ያመራል፡፡ በሳምንቱ መጨረሻ እሁድ ጨዋታውን ካደረገ በኃላም ሰኞ ወደ አዲስ አበባ እንደሚመለስ ተነግሯል፡፡
ኢትዮጵያ እና ዛምቢያ ለመጨረሻ ግዜ የተገናኙት በአቋም መለኪያ ጨዋታ በ2007 አዲስ አበባ ላይ ሲሆን ዛምቢያ 1-0 ማሸነፏ ይታወሳል፡፡