ፍቅሩ ተፈራ ለቺኔይን ፈረመ

ኢትዮጵያዊው አጥቂ ፍቅሩ ተፈራ ለህንዱ ሂሮ ሱፐር ሊግ ለሚወዳደረው ቺኔይን ፈርሟል፡፡ ያለፉትን 4 ወራት በዊትስ ቆይታ አድርጎ 1 ግብ ማስቆጠር የቻለው ፍቅሩ የውል ማረዘሚያ ስላልቀረበለት ቤድቬስት ዊትስን ለቋል፡፡ የቀድሞ የአዳማ ከነማ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኦርላንዶ ፓይሬትስ እና ሱፐር ስፓርት ዮናይትድ አጥቂ ቀጣይ ማረፉያው የህንዱ ቺኔይን ሆኗል፡፡ የህንድ ሂሮ ሱፐር ሊግን የመጀመሪያ ግብ በማስቆጠር ታሪካዊ ተጫዋች የሆነው ፍቅሩ በነፃ ዝውውር ቺኔይን ተቀሏቅሏል፡፡

የቺኔይን አሰልጣኝ የሆነው ጣላኒያዊው የዓለም ዋንጫ አሸናፊ የቀድሞ የሰማያዊዎቹ እና የኢንተር ሚላን ተከላካይ ማርኮ ማታሬዚ ˝ፍቅሩን ለ2015 የውድድር ዘመን ማስፈረም በመቻላችን በጣም ደስተኞች ነን፡፡ አምና ወጥ አቋም ያሳየው ፍቅሩ በሊጉ ከሚገኙ ምርጥ የውጭ ሃገር ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ የሊጉም አሸናፊ ነበረ፡፡ የአጨራረስ ብቃቱም የተመሰከተለት ነው፡፡ ከፍተኛ ልምድ ያላው ፍቅሩ መፈረም ለቡድናችን ጥሩ መሆም የሚጨምረው ኳሊቲ ላቅ ያለ ነው፡፡˝ ብለዋል፡፡

ፍቅሩ በበኩሉ ስለዝውውሩ አስተያየቱን ሰጥቷል ˝ለቺኔይን መፈረም በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡ ማርኮ ማታሬዚን ከመሰለ ታላቅ ተጫዋች ጋር የመስራት ዕድሉ ሲመጣ ዝም ብለህ ልትተወው አትችልም፡፡ በህንድ ፕሪምየር ሊግ መጫወት በመቻሌ ለእግርኳስ ህይወቴ የማይረሳ ነው፡፡ የመጀመሪያውን የህንድ ሊግ ግብ ያስቆጠርኩበት ዕለትን በፍፁም አልዘነጋትም፡፡ አሁን የተሻለ ተንቀሳቅሼ ክለቤን ቺኔይን ሻምፒዮን ማድረግ እፈልጋለው፡፡ ለቺኔይን መጫወት እስክጀምር ቸኩያለው፡፡˝

የህንድ ሊግ በመስከረም ወር የሚጀመር ይሆናል፡፡

ያጋሩ