የ2009 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ ደደቢት በዛሬው እለት ተጨማሪ ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረሙ ተረጋግጧል፡፡
የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ውጤት የሆነችውና ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በድሬዳዋ ከተማ ድንቅ አቋማን ያሳየችው የፊት መስመር ተጫዋቿ ትደግ ፍሰሀ ለመጪዎቹ ሁለት አመታት ለሰማያዊዎቹ ለመጫወት በዛሬው እለት ፊርማዋን አኑራለች፡፡
በቀጣይ አመታት በኢትዮጵያ የሴቶች እግርኳስ ላይ ለማንፀባረቅ የሚያስችል ችሎታ ባለቤት እንደሆነች የሚነገርላት ትደግ ከሌላዋ የቡድኑ ጎል አዳኝ ከሆነችው ሎዛ አበራ በቀጣይ አመት የሚፈጥሩት ጥምረት ከወዲሁ አጅግ አስፈሪ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል፡፡
ሌላኛዋ ቡድኑን የተቀላችው የመሀል ተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የነበረችው ሰላም ለአክም በተመሳሳይ በቀጣዮቹ ሁለት የውድድር ዘመን በደደቢት መለያ የምንመለታት ሌላኛዋ አዲስ ተጫዋች ነች፡፡
ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በአዲስ አበባ ከተማ ቡድን ውስጥ ጥሩ እንቅስቃሴን ማሳየት የቻለችው ሰላም በሶስት የመሀል ተከላካይ ለሚመራው የአሰልጣኝ ጌቱ ተሾመ የቡድን ስብስብ ጥሩ አማራጭን እንደምትሰጥ ይጠበቃል፡፡
በተመሳሳይ ከሰሞኑ በቃል ደረጃ ውሏን ለማደስ ከቡድኑ ጋር ስለመስማማቷ ሲነገርላት የነበረችው የመሀል ተከላካይዋ ዘቢብ ሀይለስላሴ በይፋ በዛሬው እለት ለቀጣዮቹ ሁለት አመታት ከክለቧ ጋር ለመቆየት ፊርማዋን አኑራለች፡፡