ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ 6 ተጫዋቾችን አስፈረመ

ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደገው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በዛሬው እለት የ5 አዳዲስ ተጫዋቾችን ፊርማ ሲያጠናቅቅ አንድ ተጫዋች በቋሚነት አስፈርሟል፡፡ እንየው ካሳሁንንም ለማስፈረም ተቃርቧል፡፡

ያለፉትን ሁለት አመታት በኢትዮ ኤሌክትሪክ ያሳለፈው ዋለልኝ ገብሬ ወደ ወልዋሎ ማምራቱ የተረጋገጠ ተጫዋች ነው፡፡ የመሀል አማካዩ በኤሌክትሪክ የአማካይ ክፍል ላይ ከበኃይሉ ተሻገር ጋር በመፈራረቅ አመዛኞቹ ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ችሏል፡፡

ቢንያም አየለ ሌላው የክለቡ ፈራሚ ነው፡፡ አዳማ ከተማ በ2007 ወደ ፕሪምየር ሊግ በተመለሰበት አመት 3ኛ ሆኖ እንዲያጠናቅቅ ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሳ ባስቆጠራቸው ወሳኝ ጎሎች የረዳ ቢሆንም ቀጥሎ ባሉት አመታት ግን ጥቂት ጨዋታዎች ላይ ብቻ ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡

ተስፋዬ ዲባባ ወደ ወልዋሎ ያመራ ሌላው ተጫዋች ነው፡፡ የቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ንግድ ባንክ የመሀል ተከላካይ በድሬዳዋ ከተማ ያለፉትን ሁለት አመታት ያሳለፈ ሲሆን በቋሚነትም ቡድኑን አገልግሏል፡፡

ክለቡ ከፕሪምየር ሊጉ በተጨማሪ ሁለት ተጫዋቾችን ከከፍተኛ ሊጉ አስፈርሟል፡፡ ግብ ጠባቂው ዘውዱ መስፍን የባህርዳር ከተማ ውሉን አጠናቆ ወደ ወልዋሎ አምርቷል፡፡ ከዚል ቀደም በቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ መተሀራ ስኳር እና ኢትዮጵያ ክለቦች በፕሪምየር ሊጉ የተጫወተው ዘውዱ ወደ ሊጉ ዳግም ተመልሷል፡፡ እዮብ ወልደማርያምም የወልዋሎ ንብረት የሆነ ተጫዋች ነው፡፡ እዮብ ወልዲያ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲገባ ቁልፉን ሚና ከተጫወተ በኋላ ክለቡን ለቆ አመቱን በአማራ ውሀ ስራ አሳልፏል፡፡

ወልዋሎ ካስፈረማቸው አዳዲስ ተጫዋቾች በተጨማሪ አሳሪ አልመሀዲን በቋሚነት አስፈርሟል፡፡ አሳሪ በውድድር አመቱ አጋማሽ ከድሬዳዋ ከተማ በውሰት አምርቶ መልካም ግልጋሎት ማበርከቱን ተከትሎ በቋሚነት ክለቡን ተቀላቅሏል፡፡

እንየው ካሳሁን ለክለቡ ለመፈረም ከስምምነት የደረሰ ተጫዋች ነው፡፡ የቀኝ መስመር ተከላካዩ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የአንድ አመት ውል ማፍረስ የሚጠበቅበት ሲሆን ውሉን በስምምነት አፍርሶ መልቀቂያውን ሲቀበል ለወልዋሎ በይፋ ይፈርማል ተብሏል፡፡

ወልዋሎ ከቀናት በፊተ የግ መስመር ተከላካዩ ሮቤል ግርማን በሁለት አመት ኮንትራት ማስፈረሙ የሚታወስ ሲሆን የበረከት አማረ ፣ ሳምሶን ተካ እና ኤፍሬም ጌታቸውን ውል ማደሱ ታውቀል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *