አፍሪካ | ሚቾ ወደ ኦርላንዶ ፓያሬትስ አምርተዋል  

ሰርቢያዊው አሰልጣኝ ሰርዮቪች ሚሉቲን ሚቾ ከደሞዝ ጋር በተያያዘ ለ6 ወራት የሰራሁበት አልተከፈለኝም በማለት ከዩጋንዳ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ሳይስማሙ መለያየታቸው ይታወቃል። አሰልጣኙ በቀጣይ ማረፊያቸው የት ይሆናል የሚለው ጥያቄ ብዙዎቹን ያነጋገረ ጉዳይ ሲሆን በመጨረሻም ማረፊያቸው የሶዌቶው ታላቅ ክለብ ሆኗል፡፡

የደቡብ አፍሪካው ሀያል ክለብ ኦርላንዶ ፓይሬትስ በመጨረሻም የ 47 ዓመቱን አሰልጣኝ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ክለብ መመለሱ ቢቢሲ ዘግቧል።

ኦርላንዶ ፓይሬትስ ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በደቡብ አፍሪካ ሊግ 11ኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን ተከትሎ ቡድኑ ዋና አሰልጣኙን እንደሚያሰናብት ቢነገርም ለስድስት ወራት ክለቡን ሲያሰለጥኑት የነበሩት ኬይል ዮንቨርት ትላንት ምሽት ራሳቸው ከክለቡ እንደለቁ አሳውቀዋል።

በ2001ዓም የዩጋንዳውን ቪላ ክለብ በማሰልጠን ወደ አፍሪካ የመጡት ሚቾ ከቪላ በኃላ ለሁለት ጊዜያት (ከ1997-98 እና 2000-2002 ) ቅዱስ ጊዬርጊስን ፣ አሁን የተቀላቀሉት ኦርላንዶ ፓይሬትስ እንዲሁም ያንግ አፍሪካን እና አልሂላል ኦምዱርማንን በክለብ ደረጃ ሲያሰለጥኑ የሩዋንዳ እና የዩጋንዳ ብሄራዊ ብድንን ደግሞ በሀገር ደረጃ ማሰልጠን ችለው ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *