በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ 6 ከኢትዮጵያ፣ ጋና እና ኬንያ ጋር የተመደበችው ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሴራሊዮን የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኟን፣ የመጓጓዣ አቅርቦት እና የቴክኒክ ሃላፊውን ማገዷን መቀመጫውን ፍሪታውን ያደረገው ፉትቦል ሴራሊዮን ድህረ-ገፅ ዘግቧል፡፡
የሴራሊዮን እግርኳስ ማህበር ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኙን ጆን ኬስተር፣ የቴክኒክ ሃላፊውን ፕሪንስ ታምባ ሞሰስ እና የመጓጓዣ አቅርቦት ሃላፊው አሊሰን ካባ ከስራ ማገዱን አስታውቋል፡፡ ቢሆንም ኬስተር እና ካባ በእግርኳስ ማህበሩ ፕሬዝደንት ኢሳ ጆንሰን ላይ ቅሬታቸው አሰምተዋል፡፡ ትውልድ እና እድገታቸው በእንግሊዝ የሆነው ኬስተር እና ሌሎች ሃላፊዎች የእግርኳስ ማህበሩን ስም እና ስራ የሚያጎድፍ ስራ በመስራታቸው ሊቀጡ እንደቻሉ የሴራሊዮን እግርኳስ ማህበር አስረድቷል፡፡
ኬስተር እና እገዳው የደረሰባቸው ሃላፊዎች ከጥቂት ሳምንታት በፊት የተነገጋገሩበት የድምፅ ቅጂ ለህዝብ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ገብተው ነበር፡፡ ኬስተር በጉዳዩ ላይ ይቅርታ ቢጠይቁም ከቅጣት ሊድኑ አልቻሉም፡፡ ኬስተር ብሄራዊ ቡድኑን በአጭር ግዜ ተረክበው በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኬንያን 2-1 ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ሴራሊዮን በእግርኳስ አስተዳደሯ ላይ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያለ ሲሆን ላለፉት አራት አመታት የእግርኳስ ማህበሩ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት አልቻለም፡፡ በአራት ዓመታት ውስጥም የሃገር ውስጥ የሊግ ውድድሮች ተደርገው አያውቅም፡፡ በሙስና የሚጠረጠሩት የማህበሩ ፕሬዝደንት ኢሳ ጆንሰን መጋቢት ላይ በነበረው የካፍ ጠቅላላ ጉባኤ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል፡፡