የክልል ክለቦች ሻምፒዮና 6ኛ ቀን ውሎ  

የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ከአንድ ቀን እረፍት በኋላ አርብ በ8 ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲካሄድ ወደ ሁለተኛው ዙር ያለፉ ተጨማሪ ክለቦችም ታውቀዋል፡፡

ምድብ 1
በዚህ ምድብ የተደረጉት ሁለት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል፡፡ ያሶ ከተማ ከ የጁ ፍሬ ወልዲያ ፣ ሾኔ ከተማ ከ ኢተያ ከተማ ያለግብ አቻ የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ናቸው፡፡ ከምድቡ የጁ ፍሬ አስቀድሞ ማለፉን ማረጋገጡ የሚታወስ ሲሆን ሽረ እንዳስላሴ ቢ ከ ኢተያ ፣ ያሶ ከ ሾኔ የሚያደርጓቸው ወሳኝ ጨዋታዎች የጁን ተከትሎ የሚያልፈውን ቡድን ይለያል፡፡

ምድብ 2
በሙሀመድ ሁሴን አሊ አል–አሙዲን ስታድየም መርካቶ አካባቢን የገጠመው ድሬዳዋ ኮተን 3-2 በማሸነፍ ወደ ሁለተኛው ዙር ማለፉን አረጋግጧል፡፡
በ16ኛው ደቂቃ ከቀኝ መስመር የተሻገረውን ኳስ በድሉ ጆቢር በግምባር ገጭቶ መርካቶ አካባቢን ቀዳሚ ያደረገ ቢሆንም መሪነታቸው ግን መቆየት የቻለው ለ4 ደቂቃ ነበር፡፡ በ20ኛው ደቂቃ አብዱ አህመድ ወደ ሳጥን የተላከውን ኳስ በቺፕ አስቆጥሮ ኮተንን አቻ አድርጓል። በ24 ደቂቃ ደግሞ ከመሀል የተሻገረውን ሰንጣቂ ኳስ ተጠቅሞ ሳሙኤል ዘሪሁን ግብ ጠባቂውን አልፎ በማስቆጠር ኮተንን ወደ መሪነት አሸጋግሯል። ለእረፍት ሰንከንዶች በቀሩበት ሰአት ከቀኝ መስመር የተላከውን ኳስ አቤል ብርሀኑ አስቆጥሮ በሁለት አቻ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

መጎሻሸም በበዛበት ሁለተኛው አጋማሽ በ58 ደቂቃ ኄኖክ አበራ ከሳጥን ውጭ አክርሮ በመምታት ማራኪ ግብ አስቆጥሮ ኮተንን ለድል አብቅቷል፡፡

በዚህ ጨዋታ ኳስ አቀባይ በበቂ ሁኔታ ባለመኖሩ ተጫዋቾች ከሽቦ ውጭ ጭምር በመውጣት ኳስ ሲያመጡ ተስተውሏል።

በዚሁ ምድብ ቀጥሎ በተካሄደው ሌላ ጨዋታ ቤንች ማጂ ፖሊስ መተከል ፖሊስን 1-0 ማሸነፍ ችሏል፡፡ ከምድቡ ድሬዳዋ ኮተን ማለፉን በማረጋገጡ እኩል 4 ነግብ እና ተመሳሳይ የግብ ልዩነት ያላቸው መርካቶ ፣ ቤንችማጂ ፖሊስ እና ቡሬ ከተማ በመጨረሻው እለት ጨዋታ ወደ ተከታዩ ዙር የማለፍ እድላቸውን ይወስናሉ፡፡

ምድብ 3
ከዚህ ምድብ አስቀድሞ ማለፉን ያረጋገጠው ናኖ ሁርቡ በደጋን ከተማ 3-0 ሲሸነፍ አሳሳ ከተማ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ፖሊስን 3-2 በማሸነፍ ብዙ ባገባ በሚለው ደጋንን በመብለጥ ወደ ሁለተኛው ዙር መቀላቀል ችሏል፡፡

ምድብ 4
አረካ ከተማ ዋልያን 2-0 በመርታት ምድቡን በ1ኝነት ማጠናቀቁን ሲያረጋግጥ ሰንዳፋ በኬ ከ ነስር ክለብ ጋር 1-1 በመለያየት አረካን ተከትሎ ወደ 2ኛው ዙር አልፏል፡፡


ይህን ሊንክ ተጭነው ሙሉውን መርሀ ግብር ፣ ውጤት እና ሰንጠረዥ ያገኛሉ፡–  የክልል ክለቦች ሻምፒዮና

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *