በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ አሰልጣኞች አንዱ በሆኑት አሰልጣኝ ከማል አህመድ ስም የተቋቋመው የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ማዕከል 1ኛ አመት መስረታ በአል እና የገቢ ማሰባሰብያ ጨዋታዎች ቅዳሜ ተጠናቀዋል፡፡
በታዳጊ ወጣቶች ፣ በሚድያዎች ፣ በጤና ቡድኖች እና በአሰልጣኙ ስር የተጫወቱ ዝነኛ ተጫዋቾች መካከል ጨዋታዎች የተደረጉ ሲሆን የገቢ ማሰባሰብያ የእራት ፕሮግራምም የመርሀ ግብሩ አካል ነበር፡፡
ከማል ከእግር ኳስ አሰልጣኝነት በክለብ ደረጃ ከ4 አመት በፊት ቢያቆሙም 150 ሴት እና ወንድ ታዳጊዎች ላይ በአሁኑ ሰአት እየሰሩ ይገኛሉ ፡፡ ይህ ማዕከል ከተመሰረተ 1 አመት የሞላው ሲሆን በግላቸው እና ከማህበረሰቡ በሚያገኙት ድጋፍ ስራቸውን እያከናወኑ ይገኛል፡፡
ይህን ማዕከል ለማጠናከር ከሐምሌ 24 ጀምሮ እስከ ቅዳሜ ሐምሌ 29 ድረስ በታዳጊ ወጣቶች ፣ በአራት የጤና ቡድኖች እና በአሰልጣኙ ረጅም ጊዜያት የሰለጠኑ ተጫዋቾች ሲደረግ የቆየ ሲሆን በተለይ ተመልካቹን ያዝናና ድንቅ ጨዋታን ያስተናገደው የቀድሞ የአሰልጣኝ ከማል ተጫዋቾች በሁለት ቡድን ተከፍለው በመቀላቀል ያደረጉት ጨዋታ ነበር፡፡ ከ1994 በፊት ስብስብ ገረሱ ሸመና ፣ አፈወርቅ ዮሀንስ ፣ ሚካኤል ወ /ሩፋኤል ፣ አዳነ ግርማ ፣ ሙሉጌታ ምህረት ፣ ብርሀኑ ጉታ ፣ አዲስአለም ተስፋዬ ፣ ሰብስቤ ደፋር ፣ ያሬድ አበጀ ፣ መሀሪ መና ፣ ዮናታን ከበደ ፣ በኃይሉ አሰፋ እና መሀመድ አህመድ ሲካተቱ ከ1996 ጀምሮ ባለው ስብስብ ፍፁም ተፈሪ ፣ ግሩም ባሻዬ ፣ ብርሀኑ ፈየራ ፣ ወንደሰን መሳ ፣ አሸናፊ አደም ፣ ዳንኤል ደርቤ ፣ ግርማ በቀለ ፣ ያሬድ ገመቹ ፣ ደረጄ ኃይሉ ፣ በረከት ይሳቅ ፣ አድናን ቃሲም እና ሌሎችም ተካተዋል፡፡
በጨዋታው ከ1994 በፊት ስም የተመደበው ቡድን በ10 ኛው ደቂቃ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ በኃይሉ አሰፋ የሰላከውን ኳስ የአሁኑ የሻሸመኔ ከተማ አሰልጣኝ የሆነው ያሬድ አበጀ ተጠቅሞ ቀዳሚ አድርጓቸዋል፡፡ ከ8 ደቂቃ በኃላም ኳስን ካቆመ በርካታ አመታት ያስቆጠረው የቀድምው የሀዋሳ ከተማ አጥቂ ወንደሰን መሳ የ1996 ቡድንን አቻ አድርጓል፡፡ የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽም 1 አቻ ተጠናቋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በቀድሞው የግራ ተከላካይነት ቦታው ተሰልፎ መጫወት የቻለው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ አዳነ ግርማ 1994 ቡድንን መሪ ሲያደርግ አዲስ አለም ተስፋዬ የግብ ልዩነቱን ከፍ አድርጓል፡፡ በኃይሉ አሰፋ የ1994 ቡድንን መሪነት ወደ 4-1 ከፍ ያደረገች ጎል ማስቆጠር ሲችል የድሬዳዋ ከተማው አጥቂ በረከት ይስሀቅ የ1996
ቡድንን ማጥበብ ችሏል፡፡ ሆኖም አዳነ ግርማ ተጨማሪ ግብ አስቆጥሮ የ1994 ቡድን 5-2 በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት ሆነዋል፡፡
በእለቱ ምሽት ላይ በሴንትራል ሀዋሳ ሆቴል የገቢ ማሰባሰብያ የእራት ግብዣ የከማል አካዳሚ መርሀግብር ፍፃሜውን አግኝቷል፡፡ በእራት ግብዣው ላይ የተለያዩ ፕሮግራሞች የተከናወነ ሲሆን በክብር እንግድነት የተገኙት አቶ ፍሰሀ ጋረደው የደቡብ ክልል እግር ኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝዳንት ፣ የደቡብ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምገስ ወንበሬ እንዲሁም የደቡብ ክልል ወጣቶች እና ሰፖርት ቢሮ የውድድር ዳይሬክተር ፣ አንጋፋ ተጫዋቾች እና የሚዲያ አካላት በተገኙበት አስተዋፅኦ ላደረጉ የምስክር ወረቀት ሲበረከት የገቢ ማሰባሰብያ መርለ ግብርምተደርጓል፡፡
በመርሀ ግብሩ አማካኝነት እስከ 1 ሚልዮን ብር ድረስ ገቢ መሰብሰቡ የተነገረ ሲሆን በአሰልጣኙ ስር ያለፉ ተጫዋቾች ገንዘብ መለገሳቸው ታውቋል፡፡ የክልሉ ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮም ማሰልጠኛ ማዕከሉ ተቋማዊ ቅርጽ እንዲኖረው እና የግንባታ ስራዎች እንዲሰሩ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገልጿል፡፡