‹‹ በናይሮቢ አጥቅተን እንጫወታለን ›› ዮሃንስ ሳህሌ

 

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ዮሃንስ ሳህሌ ዛሬ በኢንተር ኮንትኔንታል አዲስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ በመጪው ቅዳሜ ከኬንያ ጋር የሚያደርጉትን የቻን ማጣርያ የመልስ ጨዋታ በተመለከተ ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ የአሰልጣኙን ንግግሮች ለድረ-ገፃችን አንባብያን በሚሆን መልኩ እንዲህ አሰናድተነዋል፡፡

 

ስላልተመረጡ ተጫዋቾች

‹‹ ቡድኑ በሀዋሳ ልምምድ ሲያደርግ የነበረው ከረቡእ እለት ጀምሮ ቢሆንም እኔ ግን በአዲስ አበባ ስታድየም ሀሙስ እና አርብ የተደረጉትን የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ተመልክቻለሁ፡፡ በጨዋታዎቹ ያላየናቸው ወይም በጉዳት ቀንሰናቸው የነበሩትን ተጫዋቾች ለመገምገም ችያለሁ፡፡ ››

 

የተጫዋቾች የጉዳት ሁኔታ

‹‹ሳላዲን በርጊቾ የብሽሽት ጉዳት ስላጋጠመው 3 ቀን ልምምድ አልሰራም ነበር፡፡ አሁን ግን በተሟላ ጤንነት ላይ ይገኛል፡፡ በትናንቱ ልምምድ ላይ ከባድ ዝናብ ቢኖርም ተቋቁሞ ልምምዱን በአግባቡ ሰርቷል፡፡ ስዩም ተስፋዬ በትናንትናው ልምምድ ወለምታ ቢያጋጥመውም የከፋ ባለመሆኑ ለቅዳሜው ጨዋታ ይደርሳል፡፡

ወደ ናይሮቢ የሚጓዙ ተጫዋቾች

ከሁለቱ ( ቡድኑን እንደአዲስ የተቀላቀሉት ግብ ጠባቂው ምህረትአብ ገ/ህይወት እና አማካዩ ቢንያም በላይ ) በስተቀር 24ቱ የቡድን አባላት ወደ ኬንያ ይጓዛሉ፡፡ እስከ መጨረሻው ድረስ 24 ተጫዋቾች ይዘን እንቆያለን፡፡

‹‹ ከግብ ጠባቂ ጀምሮ እስከ መጨረሻው ድረስ በጨዋታው ላይ ለመሰለፍ ለሁሉም ተጫዋች ክፍት ነው፡፡ በጨዋታው ላይ ለምንተገብረው ሲስተም የሚስማሙ ተጫዋቾች ይሰለፋሉ፡፡

‹‹ለሁሉም ጨዋታ አንድ አይነት ሲስተም አንጠቀምም፡፡ ከኬንያ ጋር ባህርዳር ላይ የተጠቀምነው እና ናይሮቢ ላይ የምንጠቀመው ሲስተም የተለያየ ነው፡፡ በፊት መስመር ከሚሰለፉት ተጨዋቾች ጀምሮ የመከላከል ሲስትምን ተግባራዊ ለማድረግ እንሞክራለን፡፡ ለዛ የሚሆኑ ተጨዋቾችንም በጨዋታው ላይ እጠቀማለን፡፡ ››

ስለ ኡመድ ኡኩሪ

‹‹ ስለ ኡመድ ኡኩሪ የማውቀው ነገር የለም፡፡ በዚህም ምክንያት ለጨዋታው ተገቢ ቢሆንም በአንድ እና ሁለት ቀን ውስጥ ተቀላቅሎን እንዲጫወት አላደርግም፡፡ ››

የጨዋታ እቅድ

‹‹ መከላከልን አላምንበትም፡፡ ቡድኖች መከላከልን የሚመርጡት ማጥቃት ሲያቅታቸው እንደሆነ ነው የማምነው፡፡ ማጥቃት በተዘዋዋሪ መከላከል ስለሆነ አጥቅተን እንጫወታለን፡፡ አፈግፍገን የምንጫወት ከሆነ ተከላካዮቻችን ሊሳሳቱ ፣ በራሳቸው ላይ ግብ ሊያስቆጥሩ ወይም ፍፁም ቅጣት ምት ሊሰጥብን ይችላል፡፡››

የአማካይ ክፍሉ ክፍተት

‹‹ ቡድኑ አዲስ ነው፡፡ ስለዚህ እንደ አዲስ ነው እያዘጋጀን ያለነው፡፡ በኬንያው ጨዋታ የአማካይ ክፍሉ ላይ ክፍተት የተፈጠረው በሽመልስ አለመኖር ምክንያት ነው፡፡ በሜዳው ላይ የነበሩት ሁለቱም አማካዮች (ምንተስኖት እና ጋቶች) በመከላከል ላይ የሚያተኩሩ አማካዮች በመሆናቸው ወደፊት መሄዱ ላይ ስንቸገር ነበር፡፡ ለዛም ነው በፍጥነት ቅያሪ ያደረግኩት፡፡ ››

የአእምሮ ዝግጅት

‹‹ እኛ እዚህ 2-0 እንዳሸነፍናቸው እዛ ደግሞ ሊያሸንፉን ይችላሉ፡፡ በአዲስ ስሜት መጫወት እንዳለብን ተነጋግረናል፡፡ ውጤቱ አንድ እርምጃ ወደ ፊት አስጓዘን እንጂ ገና አልጨረስንም፡፡ በአቅም እስካልተበለጥን ድረስ እናሸንፈለን፡፡ የምንጓዘው ውጤታችንን አስጠብቀን ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ ነው፡፡

‹‹ የስነ-ልቡና ችግር ሊፈጥሩብን እደሚችሉ እንገምታለን፡፡ ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ውጪ ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ውጤት ለማግኘት በተጋጣሚ ላይ የማይፈጥሩት ችግር የለም፡፡ እኛም ይህንን ስለምናውቅ በአእምሮው ረገድ ተዘጋጅተናል፡፡ ››

ያጋሩ