በፈረንጆቹ 2003 ደቡብ አፍሪካ ላይ በተደረገ ስብሰባ ካፍ በአፍሪካ ሶስት ሃገራት የልህቀት ማዕከልን (CAF Center of excellence) ለመገንባት የተስማማ ሲሆን በኢትዮጵያ፣ ካሜሩን እና ሴኔጋል የተመረጡ ሃገራት ነበሩ፡፡ በካሜሮን የሚገኘው ማዕከል ግንባታው ተጠናቆ ወደ ስራ ሲገባ አዲስ አበባ አያት አካባቢ ያለው ማዕከል ግን ግንባታው ሳይጠናቀቅ ላለፉት 14 ዓመታት ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙት አዲሱ የካፍ ፕሬዝደንት አህመድ አህመድም የማዕከሉን ወቅታዊ ሁኔታ ተመልክተዋል፡፡
የማዕከሉ ኃላፊ አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ግንባታው በ2004 እ.ኤ.አ (1996 በኢትዮጵያ አቆጣጠር) ግንባታው የተጀመረ መሆኑን አስረድተው የኢሳ ሃያቱ አስተዳደር ግንባታው ለማጠናቀቅ ቃል ቢገባም ወደ ተግባር ለመግባት ግን መቸገሩን አስታውሰዋል፡፡ የቀድሞ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት የነበሩት ሳህሉ የመግባቢያ ሰነድ ሁለት ግዜ መፈረሙ ቢነገርም ግንባታው አሁንም አለመጠናቀቁን ተናግረዋል፡፡ የማዕከሉ አንደኛ እርከን ቢጠናቀቅም የመጫወቻ ሜዳ ሳር ንጣፉ አልተሰራም፡፡ ላለመሰራቱም የውሃ እጥረት እንደምክንያትነት ቀርቧል፡፡ ለ14 ዓመታት ምንም አግልግሎት ያልሰጡት የማዕከሉ ክፍሎች በግዜ ብዛት ጉዳት እየደረሰባቸውም ይገኛል፡፡
ማዕከሉን ተዟዙረው ያስጎበኙት አቶ ሳህሉ ማዕከሉን ገንብቶ ማጠናቀቅ እጅግ በጣም አስፈላጊ እንደሆነና ለማጠናቀቅም ተጨማሪ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ለካፍ ፕሬዝደንት አህመድ ጠቁመዋል፡፡ ፕሬዝደንት አህመድ በበሉላቸው ስለማዕከሉ ጉዳይ ወደፊት እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡ “ከዚህ ቀደም ከነበረው አስተዳደር በተለይ በጀት ዝም ብለን አንለቅም፡፡ ገንዘቡን በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ ማዋላችንን ማረጋገጥ አለብን፡፡ ከዚህ በፊት በነበረው ሁኔታም ልንጓዝ አንችልም፡፡ የፋይናንስ ግልፅነት ያስፈልገናል፡፡” ብለዋል፡፡